ግብጽ በካይሮ የኢትዮጵያ አምባሳደር ተወካይን ለማብራሪያ ጠራች
አምባሳደሩ በግድቡ የድርድር ሂደት ባላት ሚና ግብጽን መውቀሳቸው በግብጽ የውጭ ጉዳይ ባለስልጣናት ምን ያህል በጠለቀ ውስጣዊ ቀውስ ውስጥ እንደምንገኝ ለማሳየት ነው በሚል ተወስዷል
አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከሰሞኑ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የግብጽን ውስጣዊ ጉዳይ ነክተዋል በሚል ነው ተወካይ አምባሳደሩን የጠራችው
ትናንት በካይሮ የኢትዮጵያ አምባሳደር ተወካይን ለማብራሪያ መጥራቱን የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ ተወካይ አምባሳደሩን የጠራው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከሰሞኑ ከሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ጋር በተያያዘ ነው፡፡
አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው የግብጽን ውስጣዊ ጉዳይ ነክተዋል ብሏል ሚኒስቴሩ፡፡
ዘገባዎችን ዋቢ አደረግሁ እንዳለው እንደ አህራም ኦንላይን ዘገባ ከሆነ አምባሳደሩ በግድቡ የድርድር ሂደት ባላት ሚና ግብጽን አውግዘዋል፡፡
ኢትዮጵያ ግድብ የምትገነባው ግብጻውያንን ለማስራብ እና ለማስጠማት እንደሆነ በማስመሰል የህልውና ስጋት አድርጋ ማቅረቧን መኮነናቸው ግብጽ ምን ያህል በጠለቀ ውስጣዊ ቀውስ ውስጥ እንደምትገኝ ለመጠቆም ነው በሚልም ተወስዶባቸዋል፡፡
በውስጣዊ ጉዳዮቿ እንድትጠመድ ለማድረግ በማሰብ እንደተናገሩት ተደርጎም ተወስዷል፡፡
ከቃል አቀባይነታቸው በፊት በግብጽ የኢትዮጵያ አምባሳደርነት ያገለገሉት ዲና ይህን ተናግረዋል የተባለው ከሰሞኑ በሰጡት እና የግድቡ የሶስትዮሽ ድርድር የፊታችን እሁድ እንዲቀጥል የአፍሪካ ህብረትን በሊቀመንበርነት በምትመራው ደቡብ አፍሪካ ጥሪ መደረጉን ባስታወቁበት መግለጫ ነው በአህራም እንደተጠናቀረው ዘገባ፡፡
ሆኖም አምባሳደሩ በመግለጫቸው እንደተባለው ስም አልጠቀሱም፡፡ አል ዐይን አማርኛ በመግለጫው ተገኝቶ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም በጉዳዩ ላይ አስካሁን ያለው ነገር የለም፡፡ በግብጽ የውጭ ጉዳይ ባለስልጣነት ተጠሩ የተባሉት ተወካይ አምባሳደር ምላሽ ምን እንደነበርም አልታወቀም፡፡ በአህራም እና በሌሎቹ የግብጽ ሚዲያዎች ይህን በተመለከተ የቀረበ ዘገባም የለም፡፡
ሱዳን “አዲስ የድርድር መንገድ ያስፈልጋል፤ ይህ ካልሆነ አልሳተፍም” በሚል ከሶስትዮሽ ድርድሩ መውጣቷን ማስታወቋ ይታወሳል፡፡
ለዚህ ጥያቄዋ ተገቢውን ምላሽ አልሰጠኝም በሚል የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን መውቀሷም አይዘነጋም፡፡