“የኤርትራ ወታደሮች መግባት በሱዳን እና በግብጽ የተደቀነውን ችግር አስታግሷል” - አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)
ዶ/ር አረጋዊ የትግራይ ሕዝብ ራሱን ሊያደራጅ እና ስልጣን ላይ የሚወጡ ኃይሎችን ሊቆጣጠር እንደሚገባም ተናግረዋል
ሆኖም ይህ መልካም ቢሆንም “ወታደሮቹ በሕዝቡ ላይ ግፍ ሲፈጽሙ ነበር፤ ይህንንም አረጋግጫለሁ”ብለዋል አንጋፋው ፖለቲከኛ
በትግራይ ክልል በተካሄደው ሕግ የማስከበር ዘመቻ የኤርትራ ወታደሮች መግባት ሱዳን እና ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ የደቀኑትን ችግር ማስታገሱን የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበርና የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽ/ ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
“የኤርትራ ወታደሮች በሕግ ማስከበር ዘመቻው ገብተው ነበር” ያሉት ዶ/ር አረጋዊ “መተባበሩ የትም ሀገር ያለ” መሆኑን አንስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወታደር ኮሪያ፣ ኮንጎ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና ሌሎች ሀገሮች ተሰማርቶ አካባቢን ለማረጋጋት መሳተፉን ነው የገለጹት፡፡ ይህም “በሀገር ላይ የተደቀነውን ችግር ለመቋቋም አግዟል” ብለዋል፡፡
ሆኖም ይህ መልካም ቢሆንም እንኳን “ወታደሮቹ በሕዝቡ ላይ ግፍ ሲፈጽሙ ነበር፤ ይህንንም አረጋግጫለሁ” ብለዋል፡፡
“ንብረት ሲወሩ፣ ሲያፈርሱ፣ ይዘው ሲሄዱ ነበር”ም ነው ዶ/ር አረጋዊ ያሉት፡፡ ይህን መቃወማቸውንም ገልጸዋል፡፡
የሰራዊት አባላቱ “አሁን ላይ ስራቸውን ያጠናቀቁ ይመስለኛል” ያሉም ሲሆን “ከኢትዮጵያ እንዲወጡ” እየጠየቁ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ይህ የማይሆን ከሆነና ችግሩ ካልቆመ ተቃውሞ ማሰማታቸውን እንደሚቀጥሉም ነው ያነሱት፡፡
ኤርትራውያኑ “በገቡበት ዓላማ ብቻ ሊወሰኑ እንጂ ከዚያ በላይ ሊሄዱ አይገባም”ም ብለዋል አንጋፋው ፖለቲከኛ፡፡
“የትግራይ ሕዝብ ገጠር ሄደው ሲደበቁ 30 ዓመት የት ነበራችሁ? ” ብሎ ጠይቋቸዋል
ዶ/ር አረጋዊ የትግራይ ሕዝብ “ተደራጅቶ የራሱን መብት ሊያስጠብቅና ስልጣን ላይ የሚወጡ ኃይሎችን ሊቆጣጠር” እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ይህን ማድረግ ከቻለ ፓርቲያቸው (ትዴፓ) ከጎኑ እንደሚቆም ነው የገለጹት፡፡ ሆኖም ህዝቡ ትዴፓን ጨምሮ ሁሉንም የፖለቲካ ኃይል ሊቆጣጠር እንደሚገባው አስምረውበታል፡፡
“የትግራይ ሕዝብ እንደዚህ ሆነ” ብለው አሁን ላይ የሚያወሩ አካላትን መስማት እንዳስገረማቸው ያነሱት ፖለቲከኛው ሕዝቡ ችግር ያጋጠመው አሁን ብቻ እንዳልሆነ አንስተዋል፤ አካባቢው የጦር አውድማ ሆኖ ለዘመናት መቆየቱን በመጠቆም፡፡ ዋናው ችግር “ሕዝቡ የራሱን መብት አለማስጠበቁ ነው”ም ብለዋል፡፡
ይህን አድርጎ ቢሆን “ማንም ቡድን ስልጣን እየያዘ አይጫወትም ነበር” የሚሉት ዶ/ር አረጋዊ “የሕወሓት አመራሮችም በሕዝቡ ትከሻ ወደ ስልጣን መጥተው ሕዝቡን ረስተውት ነበር፤ አሁን ነው ሲሸሹ ጉሮራይ፣ ወረኢ ሄደው ሕዝቡን ያዩት” በሚል ያክላሉ ፡፡
የትግራይ ሕዝብ የሕወሓት አመራሮች “ገጠር ሄደው ሲደበቁ 30 ዓመት የት ነበራችሁ?” ብሎ እንደጠየቃቸውም ነው ያነሱት፡፡
“የተንቤን፣ የአድዋ፣ የሽሬ፣ የራያ እና የእንደርታ ሕዝብ አሁን እዚህ መጥታችሁ ምሽግ አትፍጠሩ፤ ውጡልን ነው የት ነበራችሁ እያላቸው ያለው” ሲሉም ወቅታዊ ሁኔታውን ገልጸዋል፡፡