የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዘዳንት ጃኮብ ዙማ የ15 ወራት እስር ተፈረደባቸው
ጃኮብ ዙማ በስልጣን ዘመናቸው የሙስና ወንጀልን ፈጽመዋል በሚሉ ተደራራቢ ወንጀሎች መከሰሳቸው የሚታወስ ነው
ዙማ እስሩ የተላለፈባቸው ፍርድ ቤትን ተዳፍረዋል በሚል ነው
የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዘዳንት ጃኮብ ዙማ የ15 ወራት እስር ተፈረደባቸው።
የ79 ዓመቱ ጃኮብ ዙማ በአገሪቱ እርቀ ሰላም ኮሚሽን ፍርድ ቤት መገኘት ሲኖርባቸው ባለመገኘታቸው ከህግ ተቋማት ትችቶች ሲቀርብባቸው ነበር።
ይህ እውነትን አፈላላጊ ኮሚሽን አቋቁሞ የዙማን ጉዳይ እየተመለከተ የነበረ ሲሆን ጃኮብ ዙማ ግን በዚህ ፍርድ ቤት አልቀርብም ሲሉ በይፋ ተቃውመው ነበር።
ዙማ በዚህ የኮሚሽኑ ፍርድ ቤት ለመቅረብ ፍቃደኛነት ባለመሆናቸው ባለፈ ፈርድ ቤቱ ገለልተኛ አይደለም በማለታቸው ፍርድ ቤት ተዳፍረዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
የቀድሞው ፕሬዘዳንት ዙማ ድርጊት ፍርድ ቤቱን መናቅና መድፈር በመሆኑ ሕግ አለማክበርን ያበረታታል፤ ሌሎችን ለህግ ተገዢ እንዳይሆኑ ያደርጋል የሚሉ ሀሳቦች ሲነሱ ቆይቷል።
የአገሪቱ ከፍተኛው ፍርድ ቤትም በቀድሞው ፕሬዘዳንት ድርጊት ጃኮብ ዙማ የ15 ወራት እስር ተፈርዶባቸዋል።
ዙማ እስሩ የተላለፈባቸው በተከሰሱበት የሙስና ወንጀል ቀጣይ የፍርድ ክርክር ላይ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አላከበሩም በሚል ነው።
የቀድሞው ፕሬዘዳንት የተመሰረተባቸውን የሙስና ክስ ሂደት ለመከታተል ፍርድ ቤት አልቀርብም በሚል ክሱ ተስተጓጉሎ ቆይቶ ነበር።
የቀድሞው ፕሬዘዳንት ጃኮብ ዙማ በፈረንጆቹ 1990ዎቹ አገራቸው ከፈጸመቸው የጦር መሳሪያ ግዥ ጋር በተያያዘ ሙስና ፈጽመዋል በሚል ከስልጣናቸው ከተነሱበት 2018 ዓመት አንስቶ ክሱ ሲታይ ቆይቶ ነበር።
ጃኮብ ዙማ ደቡብ አፍሪካን ከፈረንጆቹ 2009 እስከ 2017 ዓመት ድረስ በፕሬዘዳንትነት ሲመሩ ቆይተው ከህዝብ በተነሳባቸው ተቃውሞ በአሁኑ የአገሪቱ ፕሬዘዳንት ሲሪል ራማፎሳ መተካታቸው ይታወሳል።