አጣዬ ከተማ በታጣቂዎች ጥቃት “ሙሉ በሙሉ መውደሟ” ተገለፀ
ሸዋሮቢት በአንጻራዊ መረጋጋት ላይ ስትሆን ፣ ከጥቃቱ ለማምለጥ ሸሽተው የነበሩ ነዋሪዎች ወደ ቤታቸው በመመለስ ላይ ናቸው
ከጥቃት ለማምለጥ መንቀሳቀስ የማይችሉ አቅመ ደካሞች “በመኖሪያ ቤታቸው ተቃጥለው መሞታቸውን” አስተያየት ሰጪዎች ገልጸዋል
ከአንድ ወር በፊት በአማራ ክልል በሚገኙት የሰሜን ሸዋ እና የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አዋሳኝ ወረዳዎች ግጭት ተከስቶ ከ300 በላይ ሰዎች ህይወት ማለፉ አይዘነጋም።
በነዚሁ አካባቢዎች ካሳለፍነው ሐሙስ ሚያዝያ 7 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት አንስቶ ዳግም ግጭት አገርሽቶ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡
በሰሜን ሸዋ ዞን ስር የምትገኘው እና የኤፍራታ እና ግድም ወረዳ ዋና መቀመጫ የሆነችው የአጣዬ ከተማ አስተዳደር ፣ ታጣቂዎች ቀድመው ጥቃት የጀመሩባት ስፍራ ስትሆን ፣ በታጣቂዎች በተፈጸመባት ጥቃት ሙሉ በሙሉ መውደሟ ተገልጿል፡፡
አጣዬ ከተማ በአማራ ክልል ስር ካሉ ዞኖች አንዱ ከሆነው የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን በተነሱ ታጣቂዎች መውደሟን ነው የአካባቢው ነዋሪዎች ለአል ዐይን የገለጹት፡፡
በአጣዬ የተጀመረው ጥቃት ወደ ካራቆሬ ፣ ማጀቴ ፣ መኳይ ፣ ሸዋሮቢት እና ሌሎች በሰሜን ሸዋ ዞን ስር ወዳሉ ቀበሌዎች ተስፋፍቶ መቆየቱን አስተያየታቸውን ለአል ዐይን የሰጡ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ይሁንና ከፍተኛ ጉዳት ያስተናገደችው አጣዬ ከተማ ስትሆን ፣ ነዋሪዎቹ እንዳሉት በአጣዬ ከተማ የሚገኙ የመንግስት ተቋማትን ጨምሮ መኖሪያ ቤቶች እና የንግድ ተቋማት ሙሉ ለሙሉ በታጣቂዎቹ ጥቃት ወድመዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች ወደ ገጠር ቀበሌዎች ሸሽተው ተጠልለው እንደሚገኙ የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ ፣ ቤተሰብ የጠፋባቸው ሰዎች “አስከሬን ፍለጋ” ወደ ከተማዋ በመመለስ ላይ መሆናቸውንም ነግረውናል።
ከከተማዋ የሸሹ ነዋሪዎች ገጠር በሚገኙ ቀበሌዎች ባሉ ትምህርት ቤቶች ተጠልለው እንደሚገኙ እና ለረሀብ መጋለጣቸውንም አስተያየታቸውን የሰጡን የዐይን እማኞች ተናግረዋል።
በካራቆሬ እና ቆሪ ሜዳ ቀበሌዎች በተፈጸመው ተመሳሳይ ጥቃት ደግሞ “ጥቂት መኖሪያ ቤቶች እና የዕምነት ተቋማት ከጥቃቱ እንደተረፉ” ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።
ላለፉት ሶስት ቀናት በተፈጸሙ ጥቃቶች “የቆሰሉ ሰዎች በህክምና እጦት እየተሰቃዩ ናቸው” ያሉን ያነጋገርናቸው አንድ የካራቆሬ ነዋሪ “5 የተገደሉ እና 7 የቆሰሉ ሰዎችን” በዐይናቸው እንዳዩ ነግረውናል። ከታጣቂዎቹ ጥቃት ለማምለጥ መንቀሳቀስ የማይችሉ አቅመ ደካሞች “በመኖሪያ ቤታቸው ተቃጥለው መሞታቸውን”ም የዐይን እማኙ ተናግረዋል።
ሸዋሮቢት ከተማ ከትናንት ጀምሮ በመረጋጋት ላይ እነደሆነች እና ከጥቃቱ ለማምለጥ ወደ አርማኒያ ፣ ደብረሲና እና ሌሎች አጎራባች አካባቢዎች ሸሽተው የነበሩ ነዋሪዎች ወደ ቤታቸው በመመለስ ላይ መሆናቸውንም ነው ከነዋሪዎች የሰማነው።
ከትናንት ምሽት ጀምሮ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ወደ ከተሞቹ በመግባት ላይ መሆናቸውንም አስተያየት የሰጡን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረ ጻዲቅም አጣዬ ከተማ “ሙሉ ለሙሉ በታጣቂዎቹ ጥቃት መውደሟን” አረጋግጠዋል።
በዚህ ጥቃት የሞቱ ፣ የቆሰሉ ፣ የተፈናቀሉ ሰዎችን እና የወደሙ ንብረቶችን መጠን የሚያጣራ ቡድን ጥቃቱ ወደ ተፈጸመባቸው ወረዳዎች እና ቀበሌዎች መላኩን አቶ ታደሰ ለአል ዐይን ተናግረዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አሕመድ ሃሰን በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡን ብንጠይቅም አሁን መረጃ የለኝም ቆየት ብላችሁ ደውሉ ባሉን መሰረት ደግመን ጥረት ብናደርግም ስልካቸውን አላነሱልንም።
የአማራ ክልል ሰላምና ሕዝብ ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሲሳይ ዳምጤ ፣ አጣዬ ከተማ እና አካባቢው የተፈጸመው ጥቃት በ “ጽንፈኛው የኦነግ ሸኔ ቡድን” እንደሆነ መግለጻቸው ይታወሳል።
በሰሜን ሸዋ ፣ በደቡብ ወሎ እና የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ወረዳዎች ከተከሰተው የጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ የክልል እና የፌዴራል የጸጥታ ተቋማትን ጨምሮ ሶስቱንም ዞኖች ያካተተ ኮማንድ ፖስት መቋቋሙን የመከላከያ ሚኒስቴር ትናንት ምሽት ገልጿል።
ኮማንድ ፖስቱ የአካባቢውን ጸጥታ በማደፍረስ ስራ ላይ በተሰማሩ የጥፋት ቡድኖች ላይ እርምጃ በመውሰድ የህግ የበላይነት የማረጋገጥ ስራን ይሰራል ብሏል ሚኒስቴሩ።
ኮማንድ ፖስቱም 1ኛ ከደብረ ሲና እስከ ኮምቦልቻ አዋሳኝ ወረዳዎች መንገድ ላይ ፣ ከመንገዱ ግራ እና ቀኝ እስከ 20 ኪ/ሜ ውስጥ የጦር መሳርያ ይዞ መንቀሳቀስ በጥብቅ እንደሚከለከል ገልጿል።
እንዲሁም መንገድ መዝጋትን ጨምሮ አብያተ ክርስቲያናትን እና የመንግስት ተቋማትን የግለሰብ መኖርያ ቤትን እና ንብረት ማውደም ወይም ለዚህ ተግባር በተናጥልም ይሁን በቡድን መንቀሳቀስ በጥብቅ መከልከሉን በመግለጫው አስታውቋል፡፡