በአጣዬና አካባቢው የተከሰተውን ችግር ለመቅረፍ የመከላከያ ሠራዊትና የክልሉ ልዩ ኃይል እርምጃ እየወሰዱ ነው- የክልሉ መንግስት
ትናንት በካራቆሬ እና አካባቢውም ተመሳሳይ ጉዳት ያስከተለ የጸጥታ ችግር መፈጠሩን የክልሉ ሰላምና ሕዝብ ደኅንነት ቢሮ ገልጿል
የመኖሪያ ቀዬውን ለቆ ወደ ደብረሲና ያቀናውን ሕዝብ ወደ አካባቢው ለመመለስ እየተሠራ መሆኑም ተገልጿል
በአማራ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን አጣዬ ከተማ እና አካባቢው ፣ የክልሉ መንግስት “ጽንፈኛው የኦነግ ሸኔ ቡድን” እንደፈፀመው በገለጸው ጥቃት በአካባቢው የከፋ ጉዳት መከሰቱ ይታወቃል።
በትናንትናው እለትም በካራቆሬ እና አካባቢው ተመሳሳይ ጉዳት ያስከተለ የጸጥታ ችግር ተፈጥሮ እንደነበር የአማራ ክልል ሰላምና ሕዝብ ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሲሳይ ዳምጤ ለአሚኮ በሰጡት መረጃ አስታውቀዋል።
ኃላፊው “በአሁኑ ወቅትም የክልሉ ልዩ ኃይል እና መከላከያ ሠራዊት አካባቢውን ሙሉ በሙሉ ከጽንፈኛው ቡድን ነጻ ለማድረግ በቅንጅት እየሠሩ ነው” ብለዋል።
አቶ ሲሳይ አክለውም ባለፉት ቀናት የመኖሪያ ቀዬውን ለቆ ወደ ደብረሲና ያቀናውን ሕዝብ ወደ አካባቢው ለመመለስ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
የታጠቀውን ኃይል ከአካባቢው ለማፅዳት የሚከናወኑ እርምጃዎች ስለሚኖሩ ማኅበረሰቡ ከጸጥታ ኃይሉ ጎን በመቆም በጋራ ሊሠራ ይገባልም ነው ያሉት።
በተመሳሳይ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጭልጋ አካባቢ ከሰሞኑ በጸጥታ ኃይሉ እና በታጠቁ ቡድኖች መካከል ግጭት ተፈጥሮ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሲሳይ፣ ልዩ የጸጥታ ስምሪት ተሰጥቶ ችግሩን ማብረድ መቻሉን ገልጸዋል።