በሰሜን ሸዋ እና የኦሮሚያ ልዩ ዞን በሲቪል ሰዎች ላይ ባነጣጠሩ ጥቃቶች የብዙ ሰዎች ሕይወት ማለፉን ኢሰመኮ ገለፀ
ከጥቃቱ ለማምለጥ በርካታ ነዋሪዎች መኖሪያ ቤታቸውን ለቀው ወደ አጎራባች አካባቢዎች ሸሽተዋል
ያለተጠያቂነት እየተፈጸሙ ያሉትን ዘግናኝ ጥቃቶች ለማስቆም የሚያስችሉ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ኮሚሽኑ ጠይቋል
በሰሜን ሸዋ እና የኦሮሚያ ልዩ ዞን በሲቪል ሰዎች ላይ ባነጣጠሩና ብሄርን መሰረት ባደረጉ ጥቃቶች እና የአጸፋ ጥቃቶች የብዙ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሸን አስታውቋል፡፡
ጥቃቶቹ የሚወገዙ መሆናቸውን የገለፀው ኮሚሽኑ እነዚህ አሳዛኝ ክስተቶች ጥልቅ መሰረት ካላቸው ማህበረሰባዊ፣ ፖለቲካዊ እና ተቋማዊ ምክንያቶች የሚመነጩ መሆናቸውን ገልጿል፡፡ ያለተጠያቂነት እየተፈጸሙ ያሉትን ዘግናኝ ጥቃቶች በዘላቂነት ለማስቆም የሚያስችሉ እርምጃዎችን መውሰድ ግድ ይላል ሲልም ኮሚሽኑ መልዕክቱን አስተላልፏል።
መንግስትም የሰዎችን ደህንነት የመጠበቅ ግዴታውን ሊወጣ እንደሚገባ ነው ኮሚሽኑ ያሳሰበው።
በአጣዬ ከተማ ባለፈው ረቡዕ እለት አንድ መኖሪያ ቤት መቃጠሉን መነሻ በማድረግ በተፈጸሙ ጥቃቶች የሰዎች ህይወት ማለፉን አል ዐይን ዜና ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በጥቃቱ የበርካታ ንጹኃን ሕይወት ያለፈ ሲሆን በርካታ ቤቶች እና ሌሎች ንብረቶችም ወድመዋል፡፡
ጥቃት በመፈጸም ላይ ያሉት ታጣቂዎቹ የተለያዩ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን በመጠቀም ላይ ሲሆኑ በቂ የጸጥታ ኃይል በአካባቢው አለመኖሩ ፣ ባለፉት ቀናት ቀውሱን የከፋ አድርጎታል፡፡
ከጥቃቱ ለማምለጥ በርካታ ነዋሪዎች መኖሪያ ቤታቸውን ለቀው ወደ ሌሎች አጎራባች ቀበሌዎች እና ከተሞች በመሸሽ ላይ መሆናቸውንም ለአል ዐይን ዜና ተናግረዋል።
ጥቃት እየተፈጸመባቸው ወደ ሚገኝባቸው አካባቢዎች ፣ ከትናንት ምሽት ጀምሮ ተጨማሪ የጸጥታ ኃይሎች በመግባት ላይ እንደሚገኙ የአማራ ክልል ሰላምና ሕዝብ ደኅንነት ቢሮ ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን መግለጹ ይታወሳል፡፡