ህብረቱ ከአንድ ዓመት በፊት ስዋህሊ ቋንቋን የህብረቱ የስራ ቋንቋ እንዲሆን መወሰኑ ይታወሳል
አማርኛ የአፍሪካ ህብረት የስራ ቋንቋ እንዲሆን ኢትዮጵያ ጠየቀች።
44ኛው የአፍሪካ ህብረት ስራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ነው።
የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት ውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች የሚሳተፉበት ይህ የህብረቱ ሚንስትሮች ስብሰባ ዛሬ እና ነገ ይካሄዳል።
በዚህ ጉባዔ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ አፍሪካ ህብረት የአማርኛ ቋንቋን የስራ ቋንቋው እንዲያደርግ ጥያቄ አቅርበዋል።
ሚንስትሩ በንግግራቸው አክለውም "የቀድሞው አፍሪካ አንድነት ድርጅት አማርኛ አንደኛው የስራ ቋንቋ እንደሚያደርግ በወቅቱ ተነግሮ ነበር፣ ይህ እስካሁን ውሳኔ ሳያገኝ ቆይቷል" ብለዋል።
አፍሪካ ህብረት ከአንድ ዓመት በፊት በምስራቅ አፍሪካ በስፋት እሚነገረው ስዋህሊ ቋንቋን የህብረቱ የስራ ቋንቋ እንዲሆን ወስኖ ነበር።
አፍሪካ ህብረት አሁን ላይ ስዋህሊን ጨምሮ እንግሊዝኛ ፣ፈረንሳይኛ፣ አረብኛ፣ ስፓኒሽ እና ፖርቹጊዝ የስራ ቋንቋው አድርጓል።
የህብረቱ የሚንስትሮቹ ስብሰባ የፊታችን ቅዳሜ እና እሁድ በሚካሄደው የህብረቱ መሪዎች ጉባኤ የሚቀርቡ አንኳር አጀንዳዎች ላይ በመወያየት የውሳኔ ሀሳቦችን ማዘጋጀት ላይ ያተኩራል ተብሏል።
ዘንድሮው የህብረቱ መሪዎች ጉባኤ ዋነኛ ትኩረቱን በትምህርት ልማት ላይ እንደሚያደርግ ተገልጿል።