ትምህርቱ በቤጂንግ የውጭ ጥናት ዩኒቨርስቲ (BFSU) ከሚሰጡ 101 የውጭ ቋንቋ ትምህርቶች አንዱ ሆኖ የሚሰጠው
ቻይና አማርኛ ቋንቋን በመጀመሪያ ዲግሪ ልታስተምር ነው
ቻይና አማርኛ ቋንቋን በመጀመሪያ ዲግሪ ልታስተምር እንደሆነ በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታወቀ፡፡
ትምህርቱ መሰጠት የጀመረበትን ይፋዊ የመክፈቻ ስነ ስርዓት የተመለከተ መረጃን በማህበራዊ ገጹ ያጋራው ኤምባሲው ትምህርቱ በቤጂንግ የውጭ ጥናት ዩኒቨርስቲ (BFSU) መሰጠት እንደጀመረ ገልጿል፡፡
በስነ ስርዓቱ የኤምባሲው የሚኒስትር አማካሪ አቶ ሳሙዔል ፍጹም ብርሃን እና የዩኒቨርስቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ጂያን ውንጂን ንግግር አድርገዋል፡፡
ሆኖም ጉዳዩን በተመለከተ ኤምባሲው መረጃን ከማጋራት ውጪ የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም፡፡
ዩኒቨርስቲው ከቀዳሚ የቻይና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል አንዱ ነው፡፡
ሃይዲያን በተሰኘው የቤጂንግ አካባቢ የሚገኝም ሲሆን ምስራቅና ምዕራብ ብለው የተከፈሉ ሁለት ካምፓሶች አሉት፡፡
ተጠሪነቱ በቀጥታ ለሃገሪቱ ትምህርት ሚኒስቴር የሆነው ዩኒቨርስቲው በአሁኑ ሰዓት አማርኛን ጨምሮ በ101 የውጭ ሃገራት ቋንቋዎች በተለያዩ የትምህርት ደረጃዎች ያስተምራል፡፡