ለቻይናውያን ተማሪዎች የተዘጋጁ የአማርኛ ቋንቋ መማሪያ መጽሃፍት ተመረቁ
መጽሃፉ ም/ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በተገኙበት ተመርቋል
የቻይናውያን የአማርኛ መማሪያ መጽሃፉን የቤጂንግ የውጭ ጥናት ዩኒቨርሲቲ ነው ያዘጋጀው
ለቻይናውያን ተማሪዎች የተዘጋጁ የአማርኛ ቋንቋ መማሪያ መጽሃፍት መመረቃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በቤጂንግ የውጭ ጥናት ዩኒቨርሲቲ ለቻይናውያን ተማሪዎች የተዘጋጁ መጽሃፍት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በተገኙበት በቤጂንግ ተመርቋል።
ለቻይናውያን ተማሪዎች የተዘጋጁየአማርኛ መማሪያ መጽሃፍት በስነ-ስርዓቱ ሶስት የአማርኛ መመሪያ መጽሃፍት የተመረቁ ሲሆን ቻይናውያን የአማርኛ ቋንቋ ተማሪዎችም ግጥም አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በምረቃው ላይ በኢትዮጵያና በቻይና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል ግንኙነት መፍጠርና በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከቻይና የምርምር ተቋማት ጋር የእውቀት ልውውጥ ማድረግ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለውም አውስተዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በቤጂንግ የውጭ ጥናቶች ዩኒቨርሲቲ መካከል ያለው የአማርኛ ቋንቋ ትብብር የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን የበለጠ ለማጠናከር ያግዛል ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የቤጂንግ የውጭ ጥናት ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ጂያ ዌንጂያን በበኩላቸው ቋንቋው በቻይና መሰጠቱ የኢትዮጵያን ባህልና ታሪክ ለማስተዋወቅ ትልቅ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።