ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ሆነው ተሾሙ
በአፍሪካ ሕብረት የተሸሙት አዲሱ የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ በቅርብ ቀናት ወደቀጠናው እንደሚመጡ ይጠበቃል
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ባለድርሻዎች ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት፤ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆን የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ አድርገው መሾማቸውን አስታወቀ።
ይህ ውሳኔ የአፍሪካ ሕብረት በቀጠናው ያለውን ሰላምና መረጋጋት እንደሁም ጸጥታ እንዲረጋገጥ ያለውን እርምጃ እንደሚያሳይ አስታውቋል።
ተወካዩ በተለየ ሁኔታ በአፍሪካ ቀንድ ከሚገኙ የፖለቲካ ተዋናዮች ጋር እና ከባለድርሻዎች ጋር በመገናኘት ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት እንዲኖር ለማድረግ ይሰራሉ ነው የጠባለው።
የቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ይህንን ስትራቴጂያዊ ኃላፊነት በመቀበላቸው ደስተኛ መሆናቸውን የሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት አስታውቀዋል።
ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ብዙ የፖለቲካ ልምድ ያላቸው፤ የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤዎች እውን ለማድረግ እንዲሁም ለቀጣናዊ ትብብር እና ውህደት ቁርጠኛ መሆናቸውን ኮሚሽን ሊቀመንበሩ ገልጸዋል። ከዚህ ባለፈም ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ስለአፍሪካ ቀንድ ወቅታዊ ሁኔታ ጥልቅ ዕውቀት እንዳላቸውም የአፍሪካ ሕብረት ገልጿል።
በአካባቢው የሚገኙ ባለድርሻዎች እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለአዲሱ የአፍሪካ ሕብረት የቀንዱ ከፍተኛ ተወካይ ኦባሳንጆ ሁሉንም ትብብር እንዲያደጉ የሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ጥሪ አቅርበዋል።
የአፍሪካ ቀንድ አዲሱ ከፍተኛ ተወካይ በቅርብ ቀናት ወደቀጠናው እንደሚመጡ ይጠበቃል።