ሙሳ ፋኪን ጨምሮ አዲስ የተሾሙ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነሮች ቃለ መሃላ ፈጸሙ
ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም በእጩነት የቀረቡበት ምርጫ ለቀጣይ ጉባዔ ተላልፏል
አዲስ ተመራጭ ኮሚሽነሮቹ ለ4 ዓመታት የሚገለግሉ ይሆናል
ባሳለፍነው የካቲት ወር የተካሄደው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላለፉት 4 ዓመታት የህብረቱን ኮሚሽን በሊቀ መንበርነት የመሩትን ሙሳ ፋኪ ማህመትን ዳግም በሊቀ መንበርነት መምረጡ ይታወሳል።
በህብረቱ ጉባዔ ከሙሳ ፋቂ በተጨማሪም፦
አምባሳደር ባንኮል አዶዬ - የፖለቲካ ጉዳዮች እንዲሁም የሰላም እና ጸጥታ ኮሚሽነር
ጆሴፋ ሳኮ - ግብርና፣ ገጠር ልማት፣ እና ከባቢ ጉዳይ ኮሚሽነር
አንባሳደር አልበርት ሙቻንጋ - የኢኮኖሚ ልማት፣ ንግድ፣ ኢንዱስትሪ እና ማእድን ኮሚሽነር
ደ/ር አማ አቡዛይድ - የመሰረተ ልማት እና ኢነርጂ ዘርፍ ኮሚሽነር ሆነው መመረጣቸው ይታወሳል።
በዛሬው እለትም ሙሳ ፋኪን ጨምሮ አምስቱ ኮሚሽነሮች በህበረቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ቃለ መሃላ ፈፅመዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማህመትን ጨምሮ በዛሬው እለት ቃለ መሃላ የፈጸሙ ኮሚሽነሮች እስከ አውሮፓውያኑ 2024 ድረስ የሚያገለግሉ ይሆናል።
ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም በእጩነት የቀረቡበት አፍሪካ ህብረት የትምህርት፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኮሚሽነርነት እንዲሁም የጤና፣ ሰብዓዊ ጉዳይና ማህበራዊ ልማት ኮሚሽነርነት ምርጫ እስከ ቀጣዩ የመሪዎች ጉባዔ ድረስ መራዘሙ ይታወሳል።