የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የኮሮና ክትባቶችን ለማጋበስ የሚደረገውን ሩጫ አወገዙ
ራማፎዛ አደጉ በሚባሉ ሃገራት ክትባቶችን ቀድሞ ለማግኘት የሚደረገውን ጥድፊያ (vaccine nationalism) ክፉኛ ተችተዋል
ሊቀመንበሩ “ክትባቱን ሳያገኝ የሚቀር አንድም ሃገር እንዳይኖር ላቅ ያለ ትብብር ያስፈልጋል” ብለዋል
የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር እና የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ የኮሮና ክትባቶችን ለማጋበስ የሚደረገውን ሩጫ አወገዙ፡፡
ፕሬዝዳንቱ ሩጫው እንዲቆም እና ክትባቶቹ ለድሃ ሃገራት ጭምር በፍትሃዊነት እንዲደርሱ ጠይቀዋል፡፡
ራማፎዛ በበይነ መረብ በመካሄድ ላይ ባለው የዳቮስ የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ላይ ተሳትፈው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ክትባቱን ሳያገኝ የሚቀር አንድም ሃገር እንዳይኖር ላቅ ያለ ትብብር ያስፈልጋል ሲሉም ነው ፕሬዝዳንቱ የተናገሩት፡፡
አደጉ በሚባሉ ሃገራት ክትባቶችን ቀድሞ ለማግኘት የሚደረገውን ጥድፊያ (vaccine nationalism) ክፉኛ ተችተዋል፡፡
አንዳንድ ሃገራት ከፍተኛ ገንዘብን በመመደብ ክትባቶችን ቀድመው አግኝተዋል፡፡ ዜጎቻቸውን እስከ አራት ያህል ጊዜያት ለመከተብ የሚያስችሉ ክትባቶችን ለማግኘት የቻሉ ሃገራት አሉም ነው የሚባለው፡፡ ይህ በደሃ እና ክትባቱን የመግዛት አቅም ባጠራቸው ሃገራት ህዝቦች ጫንቃ የሚፈጸም ነው፡፡
ራማፎዛም ይህንኑ ነው የተቹት፡፡
በቂ ክትባቶችን ያገኙ ሃገራት እድሉን ለሌሎች እንዲለቁም ጠይቀዋል፡፡
“40 ሚሊዬን ህዝብ ላለው ሃገር 160 ሚሊዬን ክትባት አያስፈልገውም” ሲሉም ነው ፕሬዝዳንቱ ቃል በቃል የተናገሩት፡፡
አፍሪካ በክትባት ግብረ ሃይሏ በኩል 270 ሚሊዬን ክትባቶችን ለማግኘት የምትችልበት ሁኔታዎችን አመቻችታለች፡፡
ሆኖም ክትባቶቹ በቂ አይደሉም፡፡ ክትባቶች ተጨማሪ 600 ሚሊዬን በዓለም አቀፉ የክትባቶች ትብብር (ጋቪ) ኮቫክስ ስርዓት በኩል እንደሚገኙም ይጠበቃል፡፡
ከአህጉሪቱ ህዝብ 60 በመቶ ያህሉን ለመከተብ ነው የታሰበው፡፡ ለዚህም 1 ነጥብ 8 ሚሊዬን ገደማ ክትባቶች ያስፈልጋሉ፡፡