አፍሪካ ህብረት የደቡብ ሱዳን መሪዎች በተደረሰው ሰምምነት መሰረት “የገቡትን ቃል ሙሉ በሙሉ እንዲተገብሩ” ጥሪ አቀረበ
ሙሳ ፋኪ ማሃማት “በቂ ግጭቶችን ያስተናገዱት ደቡብ ሱዳናውያን አስተማማኝ ሰላም የሰፈነባት ሀገር ታስፈልጋቸዋለች” ብለዋል
የደቡብ ሱዳን የሽግግር መንግስት “ለተጨማሪ ሁለት አመታት በስልጣን ላይ እንደሚቆይ” ማስታወቁ አይዘነጋም
የደቡብ ሱዳን የሽግግር መንግስት ለተጨማሪ ሁለት አመታት ማለትም እስከ የካቲት 22 ቀን፤2025 ድረስ በስልጣን ላይ እንደሚቆይ ከቀናት በፊት ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው፡፡፡
ውሳኔውን ተከትሎ መግለጫ የሰጡት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ፤የደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች በቂ ግጭቶችን ያስተናገደው ህዝብ የተሻለ ነገር እንደሚያስፈልገው ከግምት እንዲያስገቡ አሳስቧል፡፡
በቂ ግጭቶችን ያስተናገዱት ደቡብ ሱዳናውያን አስተማማኝ ሰላም የሰፈነባት ሀገር እንደምታስፈልጋቸውም አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል ሊቀ መንበሩ ሙሳ ፋኪ ማሃማት፡፡
ሙሳ ፋኪ ማሃማት፡ የአፍሪካ ህብረት ከቀጠናው ተቋም የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) እና የተቀረው ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር በመሆን ለደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላምና ጸጥታ ሚያደረገውን ድጋፍ አጠናክሮ ላመስቀጠል ያለውን ቁርጠኝነትም አረጋግጠዋል፡፡
የደቡብ ሱዳን የሽግግር መንግስት የ"ሽግግር ጊዜ" ስልጣን ማብቂያ እንደፈረንጆቹ በ2022 የነበረ ቢሆንም በሀገሪቱ ፖለቲከኞች በተለይም በፕሬዝዳንት ሳልቫኪር እና ሪክ ማቻር (ዶ/ር) መካከል ባለው አለመስማማትና፤ የታየ ይህ ነው የሚባል ለውጥና መሻሻል ባለመኖሩ ምክንያት ወደ የካቲት 2023 መገፋቱ የሚታወስ ነው፡፡
በዚህም አላበቃም የደቡብ ሱዳን የሽግግር መንግስት ነገሮች ወደ ግጭት በማይመልሱና በሰከነ መልኩ ለማስተካከል በሚል ምክንያት ስልጣናቸውን በ24 ወራት ማራዘማቸው እያነጋገረ ነው፡፡
ፕሬዝዳንት ኪር የሽግግር መንግስት ስልጣን መራዘምን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ ነገሮች መልክ ሳይዙ ወደ ምርጫ መቸኮል አይገባም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
“በፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ በተደረገው የጋራ ውሳኔ መሰረት የሽግግር መንግስቱን ስልጣን ያራዘምነው እኔ በስልጣን ላይ መቆየት ስለምፈልግ አይደለም፡፡ ነገር ግን ዳግም ወደ ጦርነት ወደ ሚመልሰን ምርጫ ውስጥ ቸኩለን መግባት አንፈልግም”ም ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፡፡
ፕሬዝዳንቱ ለህዝባቸው ባስተላለፉት መልዕክት “የእኛ የጋራ ዓላማ እናንተን [የደቡብ ሱዳንን ሕዝብ] ወደ ሰላማዊ ምርጫ ልንወስድ ነው”ም ብለዋል፡፡
የደቡብ ሱዳን በዚህ አመት በታህሳስ ወር ሊካሄድ የታቀደው ምርጫ ማራዘማቸውም ታዲያ የሰላም ሂደቱን በሚደግፉ ምዕራባውያን ላይ ስጋት ሳይፈጥር ግን አልቀረም።
የደቡብ ሱዳንን የሰላም ሂደት በማስታረቅ ረገድ ቁልፍ ሚና የተጫወቱት አሜሪካ፣ ብሪታኒያ እና ኖርዌይ/ትሮይካ/ ውሳኔውን ውድቅ አድረግውታል፡፡
የሶስቱ ሀገራት አምባሳደሮች ለፕሬዝዳንት ኪር በጻፉት ደብዳቤ፣ ሂደቱ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ያልተማከሩበት መሆኑን አስታውቋል፡፡
ፍኖተ ካርታ ወይም የስልጣን ማራዘም ሂደቱን መደገፍ እንደምንችል የምንሰጠው ዋስትና የለም ሲሉም አስጠንቅቀዋል፡፡
ለደቡብ ሱዳን ሰላም ለፍተኛ ሚና ሲጫወት የቆየው የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ)በጉዳዩ ላይ አስካሁን ያለው ነገር የለም፡፡
እንደፈረንጆቹ 2011 ነጻነቷን የተቀዳጀችው አዲስቷ ሀገር ደቡብ ሱዳን ፤በፖለቲካ-ጎሳ አመጽ እና ስር የሰደደ አለመረጋጋት ስትታመስ መቆየቷ ይታወቃል፡፡