ደቡብ ሱዳን በዲሞክራሲያዊ ምርጫ የተመረጠ መንግስትን እንዲኖር የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ይፋ አደረገች
የፍኖተ ካርታው አዘጋጅ ኮሚቴ የሰነዱን ይዘት በተመለከተ ለፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ገለጻ አድርጓል
ፍኖተ ካርታው ደቡብ ሱዳን የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ለመተግበር ያስችላል ተብሏል
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) የደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ለመተግበር ግልጽ የሆነ ፍኖተ ካርታ ሊኖራቸው እንደሚገባ በቅርቡ ማሳሰቡ የሚታወስ ነው።
ኢጋድ የብሔራዊ አንድነት እና ፓርቲዎች የሽግግር መንግስት የምርጫ አፈጻጸምን ጨምሮ ቀሪ ተግባራትን ለማጠናቀቅ ግልጽ የሆኑ መለኪያዎች ተጨባጭ የጊዜ ሰሌዳዎችን እና ፍኖተ ካርታ እንዲያዘጋጁም ጠይቆ ነበር።
የደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች ሀገሪቱን ከገባችበት የፖለቲካ ውጥንቅጥ አውጥቶ ወደ ፊት ይወስዳታል የተባለው ፍኖተ ካርታ የሚያዘጋጅ ኮሚቴ አዋቅረው፤ ኮሚቴው የተለያዩ ስራዎች ሲያከናውን መቆየቱም አይዘነጋም።
የፍኖተ ካርታው አዘጋጅ ኮሚቴ አባላት የብሔራዊ ደህንነት ጉዳዮች የፕሬዝዳንት አማካሪው ቱት ጋትሉክ ማኒሜ፣ የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትሩ ዶ/ር ማርቲን ኤሊያ ሎሞሮ፣ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ማይክ አዪ ዴንግ እና የማስታወቂያ፣ የመገናኛ እና የፖስታ አገልግሎት ሚኒስትሩ ሚካኤል ማኩኢ ሉዌት መሆናቸው ይታወቃል።
በዚህም መሰረት ሀገሪቱ ሰላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ በማካሄድ የተመረጠ መንግስትን ለማምጣት የሚያስችል ፍኖተ ካርታን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ትናንት ከፍኖተ ካርታው አዘጋጅ ኮሚቴ መቀበላቸው የሀገሪቱ የፕሬዝዳንት ጸ/ቤት በማህበራዊ የትስስር ገጹ ላይ አስታውቋል።
ፕሬዝዳንቱ ከኮሚቴው አባላት የፍኖተ ካርታው ሰነዱን ከተቀበሉ በኋላ የሰነዱን ይዘትን በተመለከተ ገለጻ በኮሚቴው አባላት አማካኝነት ገለጻ እንደተደረገላቸውንም ነው የተገለጸው።
ከስብሰባው በኋላ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ የሰጡት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትሩ ዶ/ር ማርቲን ኤሊያ ሎሞሮ “የሰላም ስምምነት ትግበራ ያለበትን ደረጃ በመመርመር፣ የተለያዩ ተቋማትን እና ባለድርሻ አካላትን ማማከር ቀላል ሂደት አልነበረም” ብለዋል።
በመጨረሻ ግን ሀገሪቱን የሽግግር ጊዜ አብቅቶ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀት በቅተናል ሲሉም አክለዋል ዶ/ር ማርቲን ኤሊያ።