የደቡብ ሱዳን የሽግግር መንግስት ስልጣኑን ለሁለት ዓመታት ማራዘሙን አስታወቀ
ፕሬዝዳንት ኪር ጊዜው የተራዘመው“ወደ ጦርነት የሚመልሰን ምርጫ እንዳናደረግ ነው” ብለዋል
በአዲሱ ውሳኔ መሰረት የደቡብ ሱዳን ምርጫ በታህሳስ 20 ቀን፣ 2024 የሚካሄድ ይሆናል
የደቡብ ሱዳን የሽግግር መንግስት ለተጨማሪ ሁለት አመታት በስልጣን ላይ እንደሚቆይ አስታወቀ፡፡
የደቡብ ሱዳን የሽግግር መንግስት የ"ሽግግር ጊዜ" ስልጣን ማብቂያ እንደፈረንጆቹ በ2022 የነበረ ቢሆንም በሀገሪቱ ፖለቲከኞች በተለይም በፕሬዝዳንት ሳልቫኪር እና ሪክ ማቻር (ዶ/ር) መካከል ባለው አለመስማማትና፤ የታየ ይህ ነው የሚባል ለውጥና መሻሻል ባለመኖሩ ምክንያት ወደ የካቲት 2023 መገፋቱ የሚታወስ ነው፡፡
ያም ሆኖ፤ እንደፈረንጆቹ 2018 በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሰረት በተፈለገው የስምምነት ደረጃ ያልደረሱት የደቡብ ሱዳን መሪዎች፤ ያቋቋሙት የሽግግር መንግስት የስልጣን ዘመን ማራዘማቸው አስታውቋል፡፡
ፕሬዝዳንት ኪር የሽግግር መንግስት ስልጣን መራዘምን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ ነገሮች መልክ ሳይዙ ወደ ምርጫ መቸኮል አይገባም ብለዋል፡፡
“በፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ በተደረገው የጋራ ውሳኔ መሰረት የሽግግር መንግስቱን ስልጣን ያራዘምነው እኔ በስልጣን ላይ መቆየት ስለምፈልግ አይደለም፡፡ ነገር ግን ዳግም ወደ ጦርነት ወደ ሚመልሰን ምርጫ ውስጥ ቸኩለን መግባት አንፈልግም”ም ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፡፡
ፕሬዝዳንቱ ለህዝባቸው ባስተላለፉት መልዕክት “የእኛ የጋራ ዓላማ እናንተን [የደቡብ ሱዳንን ሕዝብ] ወደ ሰላማዊ ምርጫ ልንወስድ ነው” ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
የማቻር ቃል አቀባይ ፑክ ሁለቱ ባሎንግ በበኩላቸው “ምርጫው በታህሳስ 20 ቀን፣ 2024 ለማካሄድ ታቅዷል” ሲሉ መናገራቸው ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የደቡብ ሱዳን በዚህ አመት በታህሳስ ወር ሊካሄድ የታቀደው ምርጫ ማራዘማቸውም ታዲያ የሰላም ሂደቱን በሚደግፉ ምዕራባውያን ላይ ስጋት ፈጥሯል።
የደቡብ ሱዳንን የሰላም ሂደት በማስታረቅ ረገድ ቁልፍ ሚና የተጫወቱት አሜሪካ፣ ብሪታኒያ እና ኖርዌይ/ትሮይካ/ ፤ማራዘሚያው ይፋ በሆነበት ስብሰባ ላይ ሳይሳተፉ ቀርተዋል፡፡፡ ሀገራቱ የሽግግር መንግስቱን የስልጣን ዘመን መራዘም ላይ ያላቸውን ቅሬታ በተወካዮቻቸው አማካኝነት ገልጸዋል።
የሶስቱ ሀገራት አምባሳደሮች ለፕሬዝዳንት ኪር በጻፉት ደብዳቤ፣ ሂደቱ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ያልተማከሩበት መሆኑን አስታውቋል፡፡
ፍኖተ ካርታው ከዚህ በፊት ከነበሩት (የማራዘም ሂደቶች) እንዴት እንደሚለይ ማሳየት አለበት ግልጽ መሆን ያለባቸው ነገሮች አሉ ያሉት የሀገራቱ አምባሳደሮች፤ "ፍኖተ ካርታም ሆነ የስልጣን ማራዘም ጉዳይ ህጋዊ የሚባለው አካታችነቱ ታይቶ በደቡብ ሱዳን ህዝቦች እና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ነው" ብለዋል።
ፍኖተ ካርታ ወይም የስልጣን ማራዘም ሂደቱን መደገፍ እንደምንችል የምንሰጠው ዋስትና የለም ሲሉም አስጠንቅቀዋል፡፡
ለደቡብ ሱዳን ሰላም ለፍተኛ ሚና ሲጫወት የቆየው የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) በጉዳዩ ላይ አስካሁን ያለው ነገር የለም፡፡
እንደፈረንጆቹ 2011 ነጻነቷን የተቀዳጀችው አዲስቷ ሀገር ደቡብ ሱዳን ፤በፖለቲካ-ጎሳ አመጽ እና ስር የሰደደ አለመረጋጋት ስትታመስ መቆየቷ ይታወቃል፡፡