ህብረቱ አሁንም ከፍልስጤማውያን ጎን ይቆማል ብለዋል
የአፍሪካ ህብረት፤ እስራኤል በጋዛ የፈጸመችውን ተከታታይ የአየር ጥቃት አወገዘ።
የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር 6 ህጻናትን ጨምሮ ከ30 በላይ ንጹሃን ተገድለውበታል የተባለለትን የአየር ጥቃት በጽኑ በማውገዝ መግለጫ አውጥተዋል።
ሙሳ ፋኪ ማሃማት በመግለጫቸው ንጹሐንን ዒላማ መደረጋቸውን አውግዘዋል።
በእስራኤል የጸጥታ ኃይሎች የቀጠለው ህገወጥ ይዞታዎችን የማጠናከር እርምጃ ከዓለምአቀፍ ህግጋት እንደሚጻረር የገለጹም ሲሆን ፍትሐዊ እና ዘላቂ መፍትሔዎችን ለማፈላለግ የሚደረጉ ጥረቶችን ይበልጥ እንደሚያወሳስብ ነው ያሳሰቡት።
ህብረቱ አሁንም ከፍልስጤም ህዝብ ጎን መቆሙን እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ምስራቃዊ እየሩሳሌምን በዋና ከተማነት በመያዝ ራሷን የቻለችና ሉዓላዊት ሃገርን (ፍልስጤምን) ለመመስረት ለሚደረገው ቅቡልነት ያለው ጥረት ህብረቱ የማይዋዥቅ ድጋፍ እንዳለው በድጋሚ አረጋግጣለሁም ብለዋል ሙሳ ፋኪ።
የሁለቱንም ሃገራት ህልውና ከግምት ውስጥ ያስገባ አስቸኳይ ዓለም አቀፋዊ ጥረት እንደሚያስፈልግ በማስታወቅም ጥሪ አቅርበዋል።
እስራኤል በጋዛ በፈጸመቻቸው ተከታታይ የሮኬት ጥቃቶች 15 ህጻናትን ጨምሮ 44 ሰዎች መገደላቸውን ኤ.ኤፍ.ፒ ዘግቧል።
ለጊዜው ተኩስ አቁም መደረጉንም ነው ኤ.ኤፍ.ፒ የዘገበው።