አረብ ኢምሬትስ፣ አሜሪካ፣ እስራኤል እና ህንድ ለ"አብርሀም ስምምነት" ድጋፋቸውን ገለጹ
የ"አብርሀም ስምምነት"ጉዳይ ጀ ባይደን በእስራኤል እና ባህረ ሰላጤ ሀገራት ጉብኝታቸው የሚመክሩበት ዐቢይ አጀንዳ ነው
ሀገራቱ በአራቱም ሀገራት የመጀመሪያ ፊደል የተመሰረተ I2U2 የተሰኘ ቡድን ፈጥረው ዘርፈ ብዙ ትብብር እንደሚያደርጉ ይታወቃል
አረብ ኢምሬትስ፣ አሜሪካ፣ አስራኤል እና ህንድ ለ"አብርሀም ስምምነት" ያላቸውን ድጋፍ ባወጡት የጋራ መግለጫ አረጋግጠዋል።
በባህሬን እና እስራኤል መካከል የተፈረመውና የአብርሃም ስምምነት (ኢብራሂም አኮርድ) ተብሎ የሚታወቀው የሰላም ስምምነት የባህረ ስላጤው ሀገራት ከእስራኤል ጋር ሰላም እንዲፈጥሩ የሚያደረግ ስምምነት ነው፡፡
ይህ ጉዳይ (ኢብራሂም አኮርድ) ጆ ባይደን በእስራኤል እና ባህረ ሰላጤ ሀገራት ጉብኝታቸው ከሀገራቱ ከሚመክሩበት ዐቢይ አጀንዳ እንደሆነም የሚታወቅ ነው፡፡
በዚህም መሰረት I2U2 የሚል የአጋርነት ቡድን የፈጠሩት አራቱም ሀገራት (የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ አሜሪካ፣ አስራኤል እና ህንድ) በዋሽንግተን እያደረጉት ያለውን ምክክር ተከትሎ በዋይት ሃውስ በኩል ባወጡት መግለጫ ለ“አብርሀም ስምምነት” ያላቸውን ሙሉ ድጋፍ አረጋግጠዋል፡፡
"ለአብርሀም ስምምነት እና ለሌሎች የሰላም ዝግጅቶች እና ከእስራኤል ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ለሚደረጉ ጥረቶች ያለንን ድጋፍ እናረጋግጣለን” ም ነው ያሉት ሀገራቱ ባወጡት መግለጫ፡፡
በI2U2 ቡድን አባል ሀገራት መካከል የሚደረጉ ዘላቂ ኢንቨስትመንቶችን ሊያበረታቱ የሚችሉ በመካከለኛው ምስራቅ እና በደቡብ እስያ መካከል የሚደረጉ የኢኮኖሚ ትብብሮችን ማጠናከርን እንደሁም ከእነዚህ ታሪካዊ እድገቶች የሚመጡትን ኢኮኖሚያዊ እድሎች መጠቀም እንፈልጋለን ሲሉም አክለዋል፡፡
በተጨማሪም “ለእያንዳንዱ አጋር ሀገር ልዩ አስተዋጽዖ እውቅና ለሚሰጡ እንደ ኔጌቭ ፎረም ፎር ሪጅማል ኮኦፖሬሽን (አስራኤል እና ዓረብ ሀገራት በተለያዩ መስኮች የሚተባበሩበት ማዕቀፍ) ያሉ ሌሎች አዳዲስ የሀገራት ቡድኖች እንቀበላለን"ብለዋል ሀገራቱ፡፡
በአራቱም ሀገራት የመጀመሪያ ፊደል የተመሰረተው የI2U2 ፎረም፤ እንደፈረንጆቹ በጥቅምት 2021 በአራቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አነሳሽነት መመስረቱ ይታወሳል፡፡
አራቱም ሀገራት ያከተተው ቡድን I2U2 ፎረም፤ የሀገራቱ ህዝቦችን ህይወት እና የስራ ፈጠራ መንፈስ ተጠቅሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተጋረጡ ታላላቅ ፈተናዎችን ለመቅረፍ በተለይም በጋራ ኢንቨስትመንቶች እና በውሃ፣ በኢነርጂ፣ በትራንስፖርት፣ በህዋ ላይ በሚደረጉ አዳዲስ ጅምሮች ላይ እንዲሁም የጤና እና የምግብ ዋስትና ላይ ያተኮረ እንደሆነ ይነገራል፡፡