የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እስራኤል ገብተዋል
ጠቅላይ ሚኒሰትር ላፒድ “ጆ-ባይደን እስራኤል እስካሁን ካወቀቻቸው ምርጥ ወዳጆች አንዱ ናቸው” ብለዋል
ጆ ባይደን “ነፃ የሆነችውን የአይሁዶች ሀገር እስራኤል መጎብኘት ትልቅ ክብር ነው” ሲሉ ተናግረዋል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለይፋዊ የስራ ጉብኝት እስራኤል ገቡ፡፡
ፕሬዝዳንቱ ቴል አቪቭ ሲደርሱ የእስራኤል ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ያየር ላፒድ እና የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ናታሊ ቤኔት እንዲሁም በእስራኤል የአሜሪካ አምባሳደር ቶማስ አር ኒድስ ተቀብለዋቸዋል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ያየር ላፒድ በአውሮፕላን ማረፊያው በተሰናዳው መድረክ ባደረጉት ንግግር የጆ ባይደን ጉብኝት ታሪካዊ እና በግለሰብ ደረጃ ትልቅ ትርጉም ያለው ጥልቅ ነው ብለውታል።
"ይህ ጉብኝት ታሪካዊ ነው፤ ምክንያቱም በሀገሮቻችን መካከል የማይበጠስ ትስስር ለመኖሩ የሚያረጋግጥ ነው" ሲሉም ነው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ላፒድ፡፡
ላፒድ ንግግራቸው ሲቀጥሉም ጆ ባይደንን ወደ ኋላ የሚመልስ አንድ የቆየ ታሪክ አንስተዋል፡፡
“ከእስራኤል ጋር ያለዎት ግንኙነት በግለሰብ ደረጃም ሊታይ የሚችል ነው፤ ያስታውሱ እንደሆነ በአንድ ወቅት እራስዎን እንደ ጽዮናዊ ገልጸው ነበር ፤ ጽዮናዊ ለመሆን አይሁዳዊ መሆን አያስፈልግምም ብለው ነበር፤ ትክክል ነበሩ እናም እርስዎ እስራኤል እስካሁን ካወቀቻቸው ምርጥ ወዳጆች አንዱ መሆንዋ ልነግርዎት እወዳለሁ” በማለትም ጆ ባይደን ከእስራኤል ጋር ያላቸውን ቁርኝት የቆየ እንደሆነ በትዝታ መለስ አድርጎዋቸዋል፡፡
ጆ ባይደን ወደ እስራኤል ምድር በመምጣታቸው እጅግ ደስተኛ እንደሆኑ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከፕሬዝዳንቱ ጋር በሚኖራቸው ቆይታ በኢራን እና በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር በሚያደርጉት የጋራ ጥረት ላይ እንደሚመክሩ ገለጸዋል።
ጆ ባይደን በበኩላቸው “ከጓደኞቼ ጋር እንደገና መቆም እና ነፃ የሆነችውን የአይሁድን የእስራኤል መንግስት መጎብኘት ትልቅ ክብር ነው” ብለዋል።
እንደፈረንጆቹ በ1973 ከዓረብ-እስራኤል ጦርነት (ዮም ኪፑር ጦርነት) ጥቂት ወራት ቀደም ብሎ በነበሩት ጊዜያት ለመጀመሪያ ጊዜ ወጣት ሴናተር ሆነው እስራኤልን መጎብኘታቸውን ያስታወሱት ባይደን ፤ በታሪክ ከ11 የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትሮች መካከል የመጀመሪያው ከሆኑት ከጎልዳ ሜየር ጋር የመገናኘት እድል እንደነበራቸውም አውስተዋል፡፡
ጆ-ባይደን ሲተቹበት የነበረውን፤ የእስራኤል እና የፍልስጤም ግጭትን የማርገብ ጉዳይ ላይ ቅድሚያ ሰጥተው እንደሚሰሩም ተናገርዋል፡፡
"በእኔ እይታ አዲስ ባይሆንም የእስራኤላውያንም ሆነ የፍልጤማውያን የእኩልነት ነፃነት፣ ብልጽግና እና ዲሞክራሲ የወደፊት እጣ ፈንታ ለማረጋገጥ በሚጠቅመው ጉዳይ ላይ እንወያያለን ” ሲሉም ተናግረዋል።
ለእስራኤል ያላቸውን ጠንካራ ድጋፍና በሀገራቱ መካከል የሚደረገውን ትብብር ይበልጥ ለማጎልበት እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል ፕሬዝዳንት ጆ-ባይደን፡፡
ሳይንስ፣ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የኢኮኖሚ መስክ አሜሪካ እና አስራኤል በትብብር የሚሰሩባቸው መስኮች ናቸውም ብለዋል፡፡
የአሜሪካ-እስራኤል ሁለንተናዊ ግንኙነት መጎልበት ለተቀረው ዓለም አርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው ሲሉም አክለዋል፡፡
እንደፈረንጆቹ በ 2020 ከሶስት የዓረብ ሀገራት ጋር የዲፕሎማሲያዊ ስምምነቶችን ላይ የደረሰችው እስራኤል በቀጠናው ጉልህ ተሳትፎ በማድረግ ላይ መሆኗ ይታወቃል፡፡
እናም ይህ ጉብኝት ያላትን ሚና ይበልጥ ለማጠናከር የራሱ የሆነ ትልቅ አስተዋጽዖ እንደሚያበረከት ታምኖበታል፡፡