የማሊ ወታደራዊ መንግስት ስልጣኑን ለሲቪል አስተዳደር እስኪያስረክብ ድረስ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ድጋፋቸውን እንዲያቆሙ ተጠይቋል
በምዕርብ አፍሪካዊቷ አገር ማሊ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ሁለት ጊዜ በአገሪቱ ወታደሮች መፈንቅለ መንግስት ተፈጽሟል። ይህ መፈንቅለ መንግስት በ38 ዓመቱ ኮለኔል አስሚ ጎይታ አስተባባሪነት የተፈጸመ ነው።
ኮሎኔል ጎይታ ባሳለፍነው ነሀሴ ወር ላይ በወቅቱ የማሊ ፕሬዝደንት አቡበከር ኬታ ላይ በፈጸሙት መፈንቅለ መንግስት ስልጣን ቢቆጣጠሩም ፣ ከምዕራባዊያን እና አሜሪካ እንዲሁም ከአፍሪካ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ስልጣኑን ለሲቪል አስተዳደር እንዲሰጡ ከፍተኛ ጫና ከደረሰባቸው በኋላ እራሳቸውን ምክትል ፕሬዝዳንት በማድረግ አዲስ ፕሬዘዳንት እና ጠቅላላ ሚንስትር እንዲሰየም አድርገው ቆይተዋል።
ይሁንና ከሁለት ሳምንት በፊት ፕሬዝደንቱን እና ጠቅላይ ሚንስትሩን በማሰር እራሳቸውን የማሊ የሽግግር ጊዜ ፕሬዝደንት አድርገው ሾመዋል።
15 አባል አገራት ያሉት የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) ባሳለፍነው ሳምንት በጋና መዲና አክራ ከተማ በማሊ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክሮ ነበር።
በዚህ ክፍለ አህጉራዊ ስብስብ ላይ የ15 የአካባቢው አገራት ፕሬዝደንቶች እና ጠቅላይ ሚንስትሮች፣ የአውሮፓ ህብረት እና ሌሎች አገራት አምባሳደሮች እንደተገኙ ተገልጿል።
በምዕራብ አፍሪካዊቷ ማሊ በዘጠኝ ወራት ውስጥ “ሁለት ጊዜ መፈንቅለ መንግስት ያካሄዱት” እና እራሳቸውን የአገሪቱ ፕሬዝደንት አድርገው የሾሙት ኮሎኔል አስሚ ጎይታ ወደ ጋና ተጠርተው ለኢኮዋስ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚህ ስብሰባ ላይ ኮሎኔል ጎይታ ስላካሄዱት መፈንቅለ መንግስት እና ቀጣይ እቅዳቸው ነው ማብራሪያ የሰጡት።
ኢኮዋስ ከኮሎኔል አስሚ ጎይታ መስማት የፈለገው በማሊ መቼ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ አስበዋል? እንዲሁም አሁን የያዙትን ስልጣን እስከ መቼ ለሲቪል አስተዳድር ያስረክባሉ? የሚሉ ጥያቄዎችን ቢሆንም ኮሎኔል ጎይታ በዚህ ጉዳይ ላይ ምላሽ መስጠት አልቻሉም ነበር።
በዚህም ምክንያት ኢኮዋስ በማሊ በተካሄደው መፈንቅለ መንግስት ምክንያት አስተላልፎት የነበረውን ከአባልነት የማገድ ውሳኔ በድጋሚ አራዝሞ ነበር።
የአፍሪካ ህብረት የማሊን ጉዳይ እንዲከታተሉ የሾማቸው የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝደነት ጉድላክ ጆናታን ለህብረቱ የሰላም እና ደህንነት ጉባኤ ሪፖርት አቅርበዋል።
ሪፖርቱን ተከትሎ ህብረቱ ከዚህ በፊት በማሊ ላይ ጥሎት የነበረውን ከአባልነት የማገድ ውሳኔ ፣ በማሊ በህዝብ ምርጫ የተመሰረተ መንግስት ስልጣን እስኪይዝ ድረስ አራዝሟል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ለማሊ ወታደራዊ መንግስት ከሰብዓዊ መብት ጥበቃ ድጋፎች ባለፈ ሌሎች ድጋፎችን እንዳያደርጉም ህብረቱ አሳስቧል።