የማሊ ጦር አስሯቸው የነበሩትን ፕሬዝደንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር ለቀቀ
የሀገሪቱ የሽግግር ፕሬዝደንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ግለሰቦች ባለፈው ሰኞ ነበር የታሰሩት
የማሊን መፈንቅለ መንግስት የመሩት ኮሎኔል አሲማ ጎይታ ምዕራብ አፍሪካዊቷን ሀገር መምራት ጀምረዋል
ከወራት በፊት በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን የተቆጣጠረው የማሊ ወታደራዊ መንግስት የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር እና ፕሬዝደንት ካሳለፍነው ሰኞ ጀምሮ አስሯቸው ነበር።
በዚህም አሜሪካን ጨምሮ በርካታ ምዕራባዊያን አገራት መሪዎቹ እንዲለቀቁ ግፊት ሲያደርጉ ነበር።
ዓለም አቀፍ ጫና የበዛበት የማሊ ወታደራዊ መንግስት ዛሬ ማለዳ መሪዎቹን ከእስር መልቀቁን ኤኤፍፒ ዘግቧል።
ጦሩ የማሊ ፕሬዘደንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር ተገደው ከስልጣን እንዲለቁ በማድረግ በአገሪቱ ባለ ወታደራዊ ማዘዣ አስሯቸው መቆየቱም ተገልጽል።
የሀገሪቱ ጊዜያዊ ፕሬዝደንት ባህ ንዳው እና ጠቅላይ ሚኒስትር ሞክታር ኦዋን በእስር ላይ እያሉ ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው መልቀቃቸው ቢገለጽም ፣ የተባበሩት መንግስታት ይህን እርምጃ እንደማይቀበል አስታውቋል፡፡
ሁለቱ መሪዎች በ18 ወራት ውስጥ በሲቪል የሚመራ መንግስት እንዲመሰረት የማድረግ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ነበር የሽግግር መንግስቱን የሚመሩት፡፡
ይሁን እና ፕሬዝደንቱ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባልተጠበቀ መንገድ ከኃላፊነት መነሳታቸውን ተከትሎ ፣ በአውሮፓውያኑ 2020 የተካሔደውን የማሊ መፈንቅለ መንግስት የመሩት ኮሎኔል አሲማ ጎይታ ምዕራብ አፍሪካዊቷን ሀገር መምራት ጀምረዋል፡፡ ኮሎኔሉ የሽግግሩ መንግስት ምክትል ፕሬዝደንት ነበሩ፡፡