የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ኮሎኔል ጎይታ ስልጣናቸውን ለሲቪል አስተዳድር እንዲያስረክቡ ይፈልጋል
15 አባል አገራት ያሉት የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) በኮሎኔል አስሚ ጎይታ የተመራ ወታደራዊ ቡድን ባሳለፍነው ነሀሴ ወር ላይ በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን መቆጣጠሩን ተከትሎ ነበር ማሊን ከአባልነት ያገደው።
የምዕራብ አፍሪካ አገራት መሪዎች በማሊ እና ሌሎች የክፍለ አህጉሩ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በትናንትናው ዕለት በጋና መዲና አክራ መክረዋል።
በዚህ ክፍለ አህጉራዊ ስብስብ ላይ የ15 የአካባቢው አገራት ፕሬዝደንቶች እና ጠቅላይ ሚንስትሮች፣ የአውሮፓ ህብረት እና ሌሎች አገራት አምባሳደሮች እንደተገኙ ተገልጿል።
በምዕራብ አፍሪካዊቷ ማሊ በዘጠኝ ወራት ውስጥ “ሁለት ጊዜ መፈንቅለ መንግስት ያካሄዱት” እና እራሳቸውን የአገሪቱ ፕሬዝዳንት አድርገው የሾሙት ኮሎኔል አስሚ ጎይታ ወደ ጋና ተጠርተው ለኢኮዋስ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚህ ስብሰባ ላይ ኮለኔል ጎይታ ስላካሄዱት መፈንቅለ መንግስት እና ቀጣይ እቅዳቸው ነው ማብራሪያ የሰጡት።
ኢኮዋስ ከኮሎኔል አስሚ ጎይታ መስማት የፈለገው በማሊ መቼ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ አስበዋል? እንዲሁም አሁን የያዙትን ስልጣን እስከ መቼ ለሲቪል አስተዳድር ያስረክባሉ? የሚሉ ጥያቄዎችን ቢሆንም ኮሎኔል ጎይታ በዚህ ጉዳይ ላይ ምላሽ መስጠት እንዳልቻሉ ሮይተርስ ዘግቧል።
በዚህም ምክንያት ኢኮዋስ በማሊ በተካሄደው መፈንቅለ መንግስት ምክንያት አስተላልፎት የነበረውን ከአባልነት የማገድ ውሳኔ በድጋሚ ማራዘሙን ገልጿል።
የ38 ዓመቱ ኮሎኔል ጎይታ ከዘጠኝ ወር በፊት በወቅቱ የማሊ ፕሬዝደንት አቡበከር ኬታ ላይ በፈጸሙት መፈንቅለ መንግስት ስልጣን ቢቆጣጠሩም ከምዕራባዊያን እና አሜሪካ እንዲሁም ከአፍሪካ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ስልጣኑን ለሲቪል አስተዳደር እንዲሰጡ ከፍተኛ ጫና ከደረሰባቸው በኋላ እራሳቸውን ምክትል ፕሬዝዳንት በማድረግ አዲስ ፕሬዘዳንት እና ጠቅላላ ሚንስትር እንዲሰየም አድርገው ቆይተዋል።
ይሁንና ባሳለፍነው ሳምንት ፕሬዝዳንቱን እና ጠቅላይ ሚንስትሩን በማሰር እራሳቸውን የማሊ የሽግግር ጊዜ ፕሬዘዳንት አድርገው ሾመዋል።
ከቀናት በኋላም አዲስ ጠቅላይ ሚንስትር እንደሚሾሙ አዲሱ ፕሬዘዳንት ወደ ጋና ከማቅናታቸው በፊት ተናግረዋል።
ከስልጣናቸው የተነሱት ፕሬዝዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር ከሁለት ቀናት በኋላ ከእስር ተፈተዋል፡፡