እራሳቸውን የማሊ ፕሬዘዳንት አድርገው የሾሙት ኮለኔል አስሚ ጎይታ ወደ ጋና አቀኑ
ከኮለኔል ጎይታ ማብራሪያ በኋላም ኢኮዋስ የሚያሳልፈው ውሳኔ ሊኖር እንደሚችል ይጠበቃል
ኮሎኔል ጎይታ ወደ አክራ ያቀኑት በኢኮዋስ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ነው
በምዕራብ አፍሪካዊቷ ማሊ በዘጠኝ ወራት ውስጥ “ሁለት ጊዜ መፈንቅለ መንግስት ያካሄዱት” እና እራሳቸውን የአገሪቱ ፕሬዝዳንት አድርገው የሾሙት ኮሎኔል አስሚ ጎይታ ወደ ጋና አክራ ከተማ ማቅናታቸው ተሰምቷል።
ኮሎኔል ጎይታ ወደ አክራ ያቀኑት በምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ እንደሆነ ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘግቧል።
የምዕራብ አፍሪካ አገራት መሪዎች በማሊ እና ሌሎች የክፍለ አህጉሩ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለመምከር አስቸኳይ ስብሰባ እያደረገ ነው።
እራሳቸውን የማሊ ፕሬዝዳንት አድርገው የሾሙት ኮለኔል ጎይታም ለዚህ ስብሰባ ነው ጥሪ ተደርጎላቸው ወደ አክራ ያቀኑት።
በዚህ ክፍለ አህጉራዊ ስብስብ ላይ የ15 የአካባቢው አገራት ፕሬዝዳንቶች እና ጠቅላይ ሚንስትሮች፣ የአውሮፓ ህብረት እና ሌሎች አገራት አምባሳደሮች እንደተገኙ ተገልጿል።
በዚህ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ወደ ስፍራው ያቀኑት የማሊው ኮለኔል ጎይታ ስላካሄዱት መፈንቅለ መንግስት እና ቀጣይ እቅዳቸው ማብራሪያ እንደሚሰጡ ይጠበቃል።
ከኮለኔል ጎይታ ማብራሪያ በኋላም ኢኮዋስ የሚያሳልፈው ውሳኔ ሊኖር እንደሚችል ይጠበቃል።
ኮለኔል ጎይታ ከዘጠኝ ወር በፊት በምርጫ ስልጣን ላይ በነበሩት የወቅቱ ፕሬዝዳንት አቡበከር ኬታ ላይ መፈንቅለ መንግስት በማካሄድ ስልጣን ይዘው ነበር።
ከምዕራባዊያን እና አሜሪካ እንዲሁም ከአፍሪካ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ስልጣኑን ለሲቪል አስተዳደር እንዲሰጡ ከፍተኛ ጫና ከደረሰባቸው በኋላ እራሳቸውን ምክትል ፕሬዝዳንት በማድረግ አዲስ ፕሬዘዳንት እና ጠቅላላ ሚንስትር እንዲሰየም አድርገው ቆይተዋል።
ይሁንና ባሳለፍነው ሳምንት ፕሬዝዳንቱን እና ጠቅላይ ሚንስትሩን በማሰር እራሳቸውን የማሊ የሽግግር ጊዜ ፕሬዘዳንት አድርገው ሾመዋል።
ከቀናት በኋላም አዲስ ጠቅላይ ሚንስትር እንደሚሾሙ አዲሱ ፕሬዘዳንት ወደ ጋና ከማቅናታቸው በፊት ተናግረዋል።
ከስልጣናቸው የተነሱት ፕሬዝዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር ከሁለት ቀናት በኋላ ከእስር ተፈተዋል፡፡