ም/ጠ/ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ተወያይተዋል
በአፍሪካ ህብረት አመቻችነት የተጀመረው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ድርድር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ሩሲያ አስታወቀች።
የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በሞስኮ ተወያይተዋል።
በውይይቱ ወቅት የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ፤ የሕዳሴ ግድብ ድርድር በአፍሪካ ሕብረት አመቻችነት በተጀመረበት አግባብ መቀጠል እንዳለበት ሀገራቸው ጽኑ ፍላጎት እንዳላት መግለጻቸውን የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ገልጿል። ለዚህም ሩሲያ አስፈላጊውን የቴክኒክ ድጋፍ ለመስጠት ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል ብሏል ጽ/ቤቱ።
አቶ ደመቀ፤ መንግስታቸው በትግራይ ክልል እያካሄደ ያለውን የመልሶ ግንባታ እና ሰብዓዊ ድጋፍ በተመለከተ ለሩሲያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማብራሪያ መስጠታቸውም ተገልጿል።
ሰርጌ ላቭሮቭ በበኩላቸው “የኢትዮጵያ መንግስት፤ በትግራይ ክልል በኃላፊነት የወሰዳቸው እርምጃዎች እና በቁርጠኝነት የሚያከናውናቸው የሰብዓዊ ድጋፍ ተግባራት የመንግስትን የሞራል ፅናት እና የፖለቲካ ብቃት ማሳያ ናቸው” ማለታቸውን ጽ/ቤቱ ገልጿል።
በስድስተኛው ሃገር አቀፍ ምርጫ ሩሲያ በታዛቢነት እንድትሳተፍ መደረጉ “የሁለቱ ሀገራት ታሪካዊ ግንኙነት ከፍታን ያንፀባረቀ ነው “ ያሉ ሲሆን፤ ምርጫው በሰላማዊ ሁኔታ መጠናቀቁ ሞስኮን እንዳስደሰታትም ለአቶ ደመቀ መኮንን ነግረዋቸዋል ተብሏል።
ከሱዳን ጋር ያለውን የድንበር ግጭትበተመለከተ፤ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን በሰላማዊ መንገድ ለማስከበር እና ችግሮችን በዲፕሎማሲ መንገድ ለመፍታት የምትከተለውን ጤናማ አካሄድ እንደምታደንቅም ሰርጌ ላቭሮቭ ተናግረዋል ገልጸዋል ነው የተባለው።
በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚደረገውን ማንኛውንም ጣልቃ ገብነት ሩሲያ እንደማትደግፍ የገለጹት ሰርጌ ላቭሮቭ ፤ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያሉ የትብብር መስኮች ተጠናክረው ይቀጥላሉም ተብሏል።
አቶ ደመቀ፤ ሩሲያ እንደቀድሞ ሁሉ በመርህ እና የሀገር ሉዓላዊነትን ባከበረ መልኩ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ እና የምትወስደውን አቋም ማድነቃቸው ተሰምቷል። የሞስኮ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አቶ ደመቀ መናገራቸውን ጽ/ቤታቸው ገልጿል።
በቀጣይ ዓመት የአፍሪካ- ሩሲያ ፎረም አዲስ አበባ እንዲካሄድ ኢትዮጵያ ዝግጁ መሆኗን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አረጋግጠውላቸዋል ተብሏል።
አዲስ አበባ እና ሞስኮ የቆየው ታሪካዊ ግንኙነታቸው “ትርጉም ባለው ደረጃ” በተለያዩ ዘርፎች ለማስቀጠል ከስምምነት ላይ ደርሰዋል ተብሏል።