“የሕዳሴ ግድቡን መጨረስ ሁለት ጊዜ የምናስብበት ሳይሆን የምንፈጽመው ብቻ ይሆናል” ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ
“ባንዳዎች እና ባዳዎች” የኢትዮጵያ ብልጽግና ሳንካዎች መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል
የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ቁጥር አንድ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተመርቆ ስራ ጀምሯል
በ231 ሚሊዮን ዶላር የተገነባው የጣናበለስ የተቀናጀ የስኳር ፋብሪካ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተመርቆ በይፋ ስራውን ጀመረ።
በምረቃ ስነ-ስርአቱ ላይ የፌዴራል፣ የክልልና የዞን ባለስልጣናትና የስራ ሀላፊዎች እንዲሁም የአካባቢው ማህበረሰብ አባላት ተገኝተዋል።
የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ግንባታው በሜቴክ በ2003 ዓ.ም ተጀምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ተጓቶ መቆየቱ የሚታወስ ነው።
በ2010 ዓ.ም የፋብሪካው የግንባታ ስራ ለቻይናው ሲ.ኤም.ሲ.ኢ. ኩባንያ ተሰጥቶ ቀሪው ስራ በ14 ወራት ተጠናቆ ዛሬ ለምረቃ በቅቷል።
ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ በቀን 12 ሺህ ቶን ስኳር ማምረት የሚችል ሲሆን በዓመት 2 ሚለዮን 372 ሺህ ቶን ስኳር የማምረት አቅም እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡
ዛሬ የተመረቀው የጣና በለስ ስኳር ፕሮጀክት ከ60 ዓመት በፊት የተወጠነ እንደነበረ፣ ነገር ግን በፈተናዎች መደራረብ ምክንያት ሳይገነባ መቆየቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገልጸዋል።
ፋብሪካውን መርቀው የከፈቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ባንዳዎች እንደጣሊያን ጊዜ እናታቸውን ካልወቀጡ ስራ የሰሩ አይመስላቸውም” ብለዋል።
ባዳዎች ከውጭ ሆነው ኢትዮጵያ ቀና እንዳትል በማድረግ ላይ መሆናቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማሳካት በቅድሚያ ባንዳዎችን ማጥፋት እና ማጽዳት አስፈላጊ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባዳዎች ያለባንዳዎች ጥቃታቸው ስለሚቀንስ ማንዳዎችን በማጥፋት ባዳዎችን መቆጣጠር እንደሚቻል ጠቁመዋል።
ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ባደረጉት ንግግር “የሕዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ አልፎ ለሱዳንና ለግብፅ አይተኬ ትሩፋት ይዞ የሚያመጣ መሆኑን ከንግግር እና ከንድፍ ባለፈ እኛም እነሱም ስንጨርሰው የምንገነዘበው ይሆናል” ብለዋል፡፡ ይህ ግንዛቤ መሰረቱን እንዲይዝ “የሕዳሴ ግድቡን መጨረስ ሁለት ጊዜ የምናስብበት ሳይሆን የምንፈጽመው ብቻ ይሆናል” ያሉም ሲሆን “ይህ ለኛም ለነሱም የሚያስተምር እና ጠቀሜታውን የምናሳይበት ስራ ስለሆነ ፣ የጀመርነውን የግድቦች ስራ አጠናክረን እንቀጥላለን” ሲሉም አክለዋል፡፡
የአስር ዓመቱን የልማት ዕቅድ ለማሳካት ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡