“የሕዳሴው ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሌት በተያዘለት ጊዜ ይካሄዳል” - አቶ ደመቀ መኮንን
አቶ ደመቀ የተሳተፉበት በግድቡ ላይ ያተኮረ የበይነ መረብ ውይይት ተካሂዷል
የደቡብ ሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግድቡ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ የሰላም ፕሮጄክት መሆኑን ገልጿል
የሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሌት በተያዘለት ጊዜ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።
ግብጽ እና ሱዳን በተለያዩ መንገዶች በኢትዮጵያ ላይ አላስፈላጊ ጫና ለማሳረፍ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውንም አቶ ደመቀ ጠቅሰዋል፡፡
አቶ ደመቀ ይህንን ያሉት በጎረቤት ሀገራትና ታላላቅ ሀይቆች ክልል የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ባዘጋጁት የበይነ መረብ ውይይት ላይ ነው።
በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩት የደቡብ ሱዳን የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዴዔታ ደንግ ዳው ደንግ ፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ “በቀጣናው የሚገኙትን ሁሉንም ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ የሰላም ፕሮጀክት ነው” ስለማለታቸውም የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ገልጿል።
የደቡብ ሱዳን ፓርላማ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን በቅርቡ እንደሚያጸድቅም ሚኒስትር ዴዔታው ተናግረዋል፡፡ የግድቡ የሦሰትዮሽ ድርድር ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት ላይ በመድረስ እልባት እንደሚያገኝ ያላቸውን እምነትም የገለጹ ሲሆን ፣ የተፋሰሱ አባል ሀገራት የምክክሩ አካል መሆን እንደነበረባቸውም አንስተዋል፡፡
በበይነ መረቡ ውይይት ላይ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድርድር አባላት ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው ፣ ዘሪሁን አበበ ፣ ዶ/ር ዮሀንስ ገብረጻድቅ እንዲሁም በኡጋንዳው ማከሬሬ ዩኒቨርሲቲ የህግ ምሁር የሆኑት ዶ/ር ኢማኑኤል ካሲምባዜ ሌሌች የግድቡን ቴክኒካዊ እና ሕጋዊ ሁነቶች በተመለከተ የውይይት መነሻ ፅሑፍ አቅርበዋል፡፡