በአራት ልጆቿ ግድያ ተጠርጥራ የታሰረችው እናት ከ20 አመት በኋላ ነጻ ወጥታለች
የ56 አመቷ አውስትራሊያዊት ልጆቿ በተፈጥሯዊ ምክንያት ህይወታቸው ማለፉ በሳይንሳዊ ምርመራ ተረጋግጧል
“ሳይንስ ነጻ ስላወጣኝ አመሰግናለሁ” ያለችው እናት ካሳ ለመጠየቅ ተዘጋጅታለች
“የአውስትራሊያ ጨካኟ እናት” የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቷት የነበረችው እናት ከ20 አመት እስር በኋላ ነጻ ወጥታለች።
ካትሊን ፎልቢግ ከ1989 እስከ 1999 ድረስ ባሉት አመታት አራት ልጆቿን ገድላለች በሚል በ2003 ለእስር የተዳረገችው።
ልጆቹ ከ18 ቀን እስከ 18 ወራት ቆይተው ይህቺን አለም የመሰናበታቸው ጉዳይም ከግድያ ጋር የተያያዘ ነው የሚለውን ክስ አጠናክሮት ነበር።
እናት ፎልቢግ ግን ካሌብ፣ ፓትሪክ፣ ሳራህ እና ላውራ የሚል ስም የነበራቸው ልጆቿ በተፈጥሯዊ መንገድ ህይወታቸው ማለፉን ብትገልጽም ሰሚ አላገኘችም።
የየእለት ውሎዋን የምትጽፍበት (ዲያሪ)ም “የተረጋጋ ህይወት የላትም፤ ልጆቿን የገደለቻቸው እሷ ናት” ለሚለው ጉዳይ ማስረጃ ሆኖ በ2003 የ40 አመት እስራት አስፈርዶባት ነበር።
እስራቱ በይግባኝ ወደ 30 አመት ዝቅ እንዲልላት ቢደረግም “ማንም ሊሰማኝ አልቻለም ነበር” የምትለው ፎልቢንግ ባለፈው አመት ከ20 አመት እስር በኋላ በምህረት ተለቃለች።
የ56 አመቷ እናት በዛሬው እለትም ከኒው ሳውዝ ዌልስ ከፍተኛ ፍርድቤት መልካም ዜና ሰምታለች።
ፍርድ ቤቱ ካትሊን ፎልቢግ ለእስር የተዳረገችበት ማስረጃ “አሳማኝ አይደለም” የሚል ውሳኔ ማሳለፉን ነው ቢቢሲ የዘገበው።
ከዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስም ለልጆቹ ግድያ መንስኤው ተፈጥሯዊ የበራሂ (ጂን) ችግር ሊሆን ስለሚችል ምርመራ ይደረግ የሚለው የፎልቢግ ጥያቄ ነው።
በዚህም መሰረት የተደረገው ምርመራ ሁለቱ ህጻናት በአጭር ጊዜ ህይወታቸው እንዲያልፍ ምክንያት የሚሆን የበራሂ (ጂን) መለዋወጥ ሰለባ መሆናቸው መረጋገጡ ነው የተገለጸው።
ውጤቱ “የአውስትራሊያ ጨካኟ እናት” የሚለውን ተቀጽላ የሚያስፍቅና ሙሉ በሙሉ ከወንጀል ተጠያቂነት ነጻ እንድትሆን የሚያደርጋት ነው ብሏል የኒው ሳውዝ ዌልስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት።
ፎልቢግ በሲድኒ ሳግ እየተናነቃት “የበራሂ (ጂን) ሳይንስ መዘመን ልጆቼን እንዳልገደልኩ አረጋግጦልኝ ነጻ ወጥቻለሁ፤ ከ1999 ጀምሮ ነጻ የምሆንበት ህጋዊ አግባብ ቢኖርም ሰሚ አልነበረኝም” ብላለች።
“ህጻናት በድንገት እና ልብ በሚሰብር ሁኔታ ህይወታቸው እንደሚያልፍ ከማሰብ ይልቅ እኔን ተጠያቂ ማድረጉ ስለተመረጠ 20 አመታትን ያለጥፋቴ ታስሬያለው፤ የእኔን ስቃይ ማንም እንዲደግመው አልፈልግም” ስትልም ተናግራለች።
ጠበቃዋም የ56 አመቷ እናት በስህተት ለተፈጸመው እስር ካሳ ለመጠየቅ መዘጋጀቷን አስታውቀዋል።