ወሳኝ ሁነት በሰራው ስህተት በሚስቱ የተባረረው አባወራ
የሀገሪቱ ወሳኝ ሁነት በስህተት ግለሰቡ በሌላ ሀገር የሁለት ልጆች አባት መሆኑን መዝግቧል ተብሏል
በባሌ ክህደት ተፈጽሞብኛል ያለችው ሚስትም ባሏን ከመኖሪያ ቤቷ ማባረሯ ተገልጿል
ወሳኝ ሁነት በሰራው ስህተት በሚስቱ የተባረረው አባወራ።
ነገሩ የተፈጸመው በደቡብ አሜሪካዋ ቺሊ ዋና ከተማ ሳንቲያጎ ነው፡፡ ሊኦናርዶ ሴፑልቬዳ የተሰኘው ግለሰብ ለ30 ዓመታት የቆየ ባለትዳር እና የልጆች አባትም ነው።
የዚህ ግለሰብ የበኩር ልጅ ጉዳይ ለማስፈጸም ወደ ከተማዋ ወሳኝ ሁነት ተቋም ባመራበት ወቅት በሌላኛዋ ደቡብ አሜሪካ ቬንዙዌላ እህት እና ወንድም እንዳሉት ከመዝገቡ ላይ መስፈሩን ይረዳል።
ይህ ልጅም ወሳኝ ሁነትን ስለ ልጆቹ ማንነት ሲጠይቅም ልጆቹ አባቱ የወለዳቸው መሆኑን አባቱም ይህንን ማመኑን ይነግሩታል።
በጉዳዩ የተገረመው ይህ ልጅም ለእናቱ መናገሩን ተከትሎ አባትየው በቤተሰቡ ላይ ክህደት እንደፈጸመ ተነግሮት መኖሪያ ቤቱን ለቆ እንዲወጣ መደረጉ ተገልጿል።
ይሁንና ከመኖሪያ ቤቱ የተባረረው ይህ አባወራ ስለተባለው ጉዳይ እንደማያውቅ ልጆችንም እንዳልወለደ ቢያስረዳም የሚሰማው አልተገኘም።
ምዝገባውን ከፈጸመው ወሳኝ ሁነት ተቋም ጋር በተደረገ ተከታታይ ውይይት ምዝገባው ስህተት መሆኑ ይረጋገጣል። ስህተቱ የተፈጸመውም የተቋሙ ሰራተኛ ተመሳሳይ ስም ያላቸውን ሰዎች ሲመዘግብ የፈጸመው ስህተት እንደሆነ ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል።
ተከድተናል ባሉ ቤተሰቦቹ ከቤት የተባረረው አባወራ ወደቤቱ የተመለሰ ሲሆን የቤተሰብ ህይወቱ እንዲመሰቃቀል ባደረገው ተቋም ላይም ክስ እንደሚመሰርት አስታውቋል።