በአሜሪካ በስህተት ለ33 ዓመታት የታሰረው ግለሰብ ከእስር ተለቀቀ
ግለሰቡ በ22 ዓመቱ ላይ ታስሮ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ 55 ዓመት ሆኖታል
ከእስር የተለቀቀው ግለሰብ ቀሪ ሕይወቱን ያለጸጸት መኖር እንደሚፈልግ ተናግሯል
በአሜሪካ በስህተት ለ33 ዓመታት የታሰረው ግለሰብ ከእስር ተለቀቀ፡፡
የካሊፎርኒያው ዳንኤል ሳልዳና የ22 ጎረምሳ እያለ ነበር በግድያ ሙከራ ወንጀል ተጠርጥሮ ለእስር የተዳረገው፡፡
ይህ ግለሰብ በፈረንጆቹ 1990 ላይ በሎስ አንጀለስ ባለ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ላይ በተፈጸመ የጦር መሳሪያ ጥቃት ተጠርጥሮ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደዋለ ተገልጿል፡፡
ዳንኤል ሳልዳናም በተጠረጠረበት ወንጀል የ45 ዓመት እስር የተፈረደበት ሲሆን ወንጀሉን እንዳልፈጸመ ለፖሊስ እና ለፍርድ ቤት ቢናገርም የሰማው አልነበረም፡፡
የተፈረደበትን የእስር ጊዜያት እየፈጸመ እያለ ከ33 ዓመት እስር በኋላ ወንጀሉን አልፈጸምክም ተብሎ ከእስር ተለቋል ሲል ዩኤስቱዳይ ዘግቧል፡፡
ከእስር በመለቀቁ በደስታ ውስጥ ያለው ዳንኤልም “ሁሌ ከእንቅልፍ ስነቃ ወንጀሉን እንዳልፈጸምኩ ከህሊናዬ ጋር መታገል ሰልችቶኝ ነበር” ሲል ተናግሯል፡፡
ይህ ቀን በመምጣቱ ደስተኛ ነኝ የሚለው ዳንኤል ሳልዳና ቀሪ ሕይወቴን ያለጸጸት በነጻነት መኖረ እንደሚፈልግ አስታውቋል፡፡
የካሊፎርኒያ አቃቢ ህግ ዳንኤል ሳልዳና ከ33 ዓመት በፊት በትምህርት ቤቱ ላይ የጦር መሳሪያ ጥቃት ሲፈጸም በአካባቢው እንዳልነበር ተናግሯል ተብሏል፡፡
ዳንኤል በወቅቱ ለፍርድ ቤቱ ጥቃት በተፈጸመበት ሰዓት በአንድ የኮንስትራክሽን ስራ ላይ እንደነበር አስረድቶ የነበረ ቢሆንም ያመነው አካል እንዳልነበር ተገልጿል፡፡