የ30 አመት እስራት የተፈረደበት ጣሊያናዊ ክብደቱ ከእስር አስፈትቶታል
ግለሰቡ ፍቅረኛውን በመግደል ተከሶ ዘብጥያ በወረደ አንድ አመት ውስጥ 80 ኪሎግራም ጨምሯል
የሟች ቤተሰቦች እስር ቤቱ ለታራሚው የሚመች ምግብ አያቀርብም በሚል እንዲፈታ መወሰኑ “አሳፋሪ” ነው ብለዋል
በፍቅረኛው ግድያ የ30 አመት የተፈረደበት ጣሊያናዊ ክብደቱ ከልክ በላይ እየጨመረ መሄዱን ተከትሎ ከእስር ቤት እንዲለቀቅ ተወስኗል።
ዲሚትሪ ፍሪካኖ በፈረንጆቹ 2017 ኢሪካ የተሰኘች ፍቅረኛውን 57 ጊዜ ደብድቦ መግደሉ ተረጋግጦ ነው በ2022 የ30 አመት እስር የተወሰነበት።
ግለሰቡ መኝታ ቤት ውስጥ ተመግቦ የጣላቸው የምግብ መያዣዎች ከፍቅረኛው ጋር ያስነሳው የቃላት ልውውጥ ለግድያው መነሻ እንደነበር በምርመራው ተረጋግጧል።
አብዝቶ የሚመገበው ዲሚትሪ ባለፈው አመት ወደ ዘብጥያ ሲወርድም 120 ኪሎግራም ይመዝን ነበር ተብሏል።
ባለፉት 12 ወራትም 80 ኪሎግራም ጨምሯል የሚሉ የህክምና ባለሙያዎች ከልክ ያለፈው ውፍረት ለከባድ የጤና እክል እየዳረገው ነው ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ዲሚትሪ በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ለመንቀሳቀስም ዊልቼር እና ክራንች ለመጠቀም ተገዷል።
በማረሚያ ቤቱ ክብደቱን ለመቀነስ የሚያስችሉ ዝቅተኛ ካሎሪ ያላቸው ምግቦች ማቅረብ እንደማይቻል የጠቀሱ ባለሙያዎች ያቀረቡትን አቤቱታ የተመለከቱ ዳኞችም ግለሰቡ ከማረሚያ ቤቱ ወጥቶ የቁም እስረኛ እንዲሆን ወስነዋል ብሏል የጣሊያኑ ኮሬር ዴላ ሴራ ጋዜጣ።
ዲሚትሪ ቤላ በተባለችው የሀገሪቱ ከተማ የቁም እስረኛ ሆኖ ተገቢው የህክምና ክትትል ይደረግለት የሚል ውሳኔ መተላለፉም ነው የተነገረው።
ምንም እንኳን ዲሚትሪ ፍሪካኖ ክብደቱና ጤናው ሲስተካከል ዳግም ወደ ማረሚያ ቤት ይመለሳል ቢባልም ውሳኔው የሟች ፍቅረኛውን ቤተሰቦች እጅጉን አስቆጥቷል።
የሟች ኢሪካ አባት የቁም እስር ውሳኔውን “አሳፋሪ ነው፤ የማፊያ ቡድን መሪዎች ራሱ እንዲህ አይነት እንክብካቤ ያገኛሊ ብዬ አልጠብቅም” በሚል ተቃውመውታል።