የአውትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሀገራቸው ከፈረንሳይ ጋር ያላትን ግንኙነት ማደስ እንደሚፈልጉ ገለጹ
ፕሬዝዳንት ማክሮን በበኩላቸው ሻክሮ የነበረው የሀገራቱ ግንኙነት እንዲሻሻል የፈረንሳይ ፍላጎት ነው ብለዋል
አውስትራሊያ ከፈረንሳይ ጋር የነበራትን የባህር ሰርጓጅ መርከቦች ግዥ ውል መሰረዟን ተከትሎ የሀገራቱ ግንኙነት መሻከሩ ይታወሳል
የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዝ ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑዌል ማክሮን ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማደስ እንደሚፈልጉ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ይህንን ያሉት በዛሬው እለት በፓሪስ ተገኝተው ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ጋር ሀገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ነበረበት መልካም የሚባል ሁኔታ ለመመለስ ከመከሩ በኋላ መሆኑ የፈረንሳዩ የዜና ወኪል /ኤ.ኤፍ.ፒ/ ዘግቧል፡፡
ፕሬዝዳንት ማክሮን በበኩላቸው ሻክሮ የነበረው የሀገራቱ ግንኙነት እንዲሻሻል የፈረንሳይ ፍላጎት ነው ብለዋል፡፡
አውስትራሊያ ከፈረንሳይ ጋር የነበራትን የባህር ሰርጓጅ (ሰብማሪን) መርከቦች ግዥ ውል መሰረዟን ተከትሎ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መሻከሩ ይታወሳል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑዌል ማክሮን አውስትራሊያ ከፈረንሳይ ጋር የነበራት የ37 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ዶላር የባህር ሰርጓጅ (ሰብማሪን) መርከቦች ግዥ ስምምነት በመሰረዝ ከአሜሪካና ብሪታኒያ ጋር አዲስ ወታደራዊ ማእቀፍ ስምምነት በመፈራረሟ ተበሳጭተው ነበር።
የፈረንሳዩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄያን ለቨድሪያን በወቅቱ በሰጡት አስተያየት የአውስትራሊያ ተግባር “በወዳጅ ከጀርባ በስለት እንደመወጋት ነው” ብለው ነበር።
አውስትራሊያ ስምምነቱን ሰርዛ ከአሜሪካ እና ከብሪታኒያ ጋር አዲስ የወታደራዊ ማእቀፍ ስምምነት በመፈረሟ የተበሳጨችው ፈረንሳይ በአሜሪካ እና በአውስትራሊያ የሚገኙ አምባሳደሮቿን ጠርታ እንደበረም ይታወሳል።
አውስትራሊያ እና ፈረንሳይ በአውሮፓውያኑ በ2016 ነበር የባህር ሰርጓጅ (ሰብማሪን) መርከቦች ግዢ ስምምነት የተፈራረሙት፤ በስምምነቱ መሰረትም ፈረንሳይ 12 የባህር ሰርጓጅ (ሰብማሪን) መርከቦች ለአውስትራሊያ ለመገንባ ተስማምተው ነበር።