የአውራምባ ማህበረሰብ አስተሳሰብ ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት የፖለቲካ ችግር መፍትሄ ሊሆን ይችላል ተበለ
የአውራምባ ማህበረሰብ ከተመሰረተ 50 ሞልቶታል
የአውራምባ ማህበረሰብ በ1964 ዓ.ም በዙምራ ኑሩ አስተባባሪነት በ19 ሰዎች ነበር የተመሰረተው
የአውራምባ ማህበረሰብ አስተሳሰብ ቢተገበር ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት የፖለቲካ ችግር መፍትሄ ሊሆን ይችላል ተበለ፡፡
“የሰው ልጅ ክቡር ነው” በሚል አስተሳሰቡ የሚታወቁት ዙምራ ኑሩ ይሄንን አስተሳሰባቸውን ይዘው በብዙ ቦታዎች ከዞሩ በኋላ አሁን ባሉበት በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ እሳቸውን ጨምሮ ከሌሎች 18 ሰዎች ጋር እንደመሰረቱት ይናገራሉ፡፡
በ1964 ዓ.ም በነዚህ ሰዎች የተመሰረተው ይህ ማህበረተሰብ 50ኛ የምስረታ በዓላቸውን በማክበር ላይ ናቸው፡፡
በዓሉን መሰረት በማድረግም በአዲስ አበባ መስራቹ የክብር ዶክተር ዙምራ ኑሩ፣ ማህበረተሰብ ተመራማሪዎች እና አጥኚዎች በተገኙበት ውይይት ተካሂዷል፡፡
በዚህ የውይይት ፕሮግራም ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት የማህበረሰብ ተመራማሪው ዶክተር ክንደለም ደምጤ የአውራምባ ማህበረሰብ አስተሳሰብ የሰው ልጅን መሰረት ያደረገ በመሆኑ አሁን ላለንበት ችግር መፍትሄ ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡
“ይህ ማህበረሰብ ለሰው ልጅ ክቡርነት ትልቅ ዋጋ አለው፣ ከልጅ አስተዳደግ፣ ስራን ከጾታ ጋር ለይተው ማየታቸው፣ አቅመ ደካሞችን ወገኔ ዘሬ ሳይሉ መርዳታቸው ከሌላው ማህበረሰብ ለየት ያደርጋቸዋል “ ብለዋል ዶክተር ክንዳለም፡፡
“አሁን ያለንበት ሀገራዊ የፖለቲካ ችግር ራስ ወዳድነት እና ስግብግብነት ስላለ የመጣ ነው“ የሚሉት ዶክተር ክንዳለም ይህ አስተሳሰብ ድንገት መተግበር የሚችል ባይሆንም በቀጣይ የአውራምባ ማህበረሰብ አመለካከትን ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዲሰፋ ቢደረግ አስተሳሰቡ ለችግሮቻችን መፍትሄ ሊሆን ይችላልም ብለዋል፡፡
ይህ ማህበረሰብ የተመራማሪዎችን፣ ጎብኚዎችን እና የሌሎች ማህበረሰቦችን ትኩረት የሳበው የተለየ ሀብት ስላለው ሳይሆን አመለካከታቸውን ወደ ተግባር ስለቀየሩ መሆኑንም ዶክተር ክንዳለም አክለዋል፡፡
እንደ ዶክተር ክንዳለም ገለጻ አውራምባ የራሱ የሖነ ኢትዮጵያዊ የአስተሳሰብ ፍልስፍና ሲሆን ስርዓተ የጾታ እኩልነት የሰው ልጅ ክቡርነት ዓለም አቀፋዊ አስተሳስብ ቢሆንም ዙምራዎች ከሌላው ማህበረሰብ የሚለዩት የሚያምኑበትን አስተሳሰብ በመተግበራቸው ብቻ መሆኑንም ተመራማሪው ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም የዚህ ማህበረሰብ ታሪክ እና እሴቶች በሚገባ ተጠንተው መሰነድ እንዳለባቸውም ዶክተር ክንዳለም አሳስበዋል፡፡
የአውራምባ ማህበረሰብ መስራች የሆኑት ዙምራ ኑሩ ላደረጉት የአስተሳሰብ ለውጥ ጁማ ዩንቨርሲቲ በ2009 ዓ.ም የክብር ዶክትሬት ድግሪ መሰጠታቸው ይታወሳል፡፡