የቀድሞ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ፓርክ ጉን ሃይ በምህረት ከእስር ተለቀቁ
ፓርክ በትከሻቸው እና ወገባቸው ላይ ባጋጠማቸው ህመም በሴኡል በሚገኝ ሆስፒታል ሲታከሙ ቆይቷል
ፓርክ ከእስር ከተለቀቁ በኋላ ለፕሬዝዳንት እንደሚደረገው የደህንነት ጥበቃ የሚደረግላቸው ይሆናል ተብሏል
የቀድሞ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ፓርክ ጉን ሃይ በምህረት ከእስር ተለቀቁ፡፡
የቀድሞው የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ፓርክ ጊዩን ሃይ፤ በፕሬዝዳንት ሙን ጃኢን በተደረገላቸው ልዩ ይቅርታ ከእስር ነጻ ወጡ፡፡
በሙስና ተከሰው ላለፉት 57 ወራት በእስር የቆዩት ፓርክ፤ በትከሻቸው እና ወገባቸው ላይ ባጋጠማቸው ህመም ምክንያት ከአንድ ወር በላይ በሴኡል በሚገኝ ሆስፒታል ሲታከሙ ቆይቷል፡፡
የፓርክ ህምም ከግምት ያስገቡ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሙን ጃኢን ፓርክ በሆስፒታል ሳሉ የምህረት ሰርተፍኬት እንዲያገኙ ማድረጋቸውንም ነው የሲጂቲኤን ዘገባ የሚያመለክተው፡፡
የ69 አመቷ አዛውንት እስከ የካቲት 2 ድረስ በሆስፒታሉ ህክምና እየተከታተሉ ለመቆየት እቀድ ነበራቸውም ተብሏል፡፡
ከሳምንት በፊት የደቡብ ኮሪያ የፍትህ ሚኒስቴር ፓርክ ለአዲሱ አመት የፕሬዝዳንት ሙን ልዩ የምህረት አዋጅ ዝርዝር ውስጥ መካተታቸው ማስታወቁ አይዘነጋም።
ከሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው ፤ የፓርኩ የጤና ሁኔታ እያሽቆለቆለ መምጣቱ የምህረት ውሳኔውን ለመወሰን እንደ ምክንያት ተደርጎ ተወስዷል፡፡
ፓረክ በስልጣን ዘመናቸው ፈጽመውታል በተባለ ከባድ የሙስና ወንጀል ምክንያት የ22 ዓመታት እስር ተፈርዶባቸው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
ፓርክ ከእስር ከተለቀቁ በኋላ ለፕሬዝዳንት እንደሚደረገው የደህንነት ጥበቃ የሚደረግላቸው ይሆናል ተብሏል፡፡ይሁን እንጅ እንደ እንደ በስልጣን ዘመናቸው ፕሬዝዳንት ሆነው ያግኙዋቸው የነበሩ ሌሎች ልዩ መብቶች የማይኖሯቸው ይሆናል፡፡