የደቡብ አፍሪካው ጸረ-አፓርታይድ ታጋይ ዴዝሞንድ ቱቱ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ
በስርዓተ ቀብሩ ላይ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዘዳንትን ጨምሮ ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል
ስርዓተ ቀብሩ የተፈጸመው ለዓመታት ባገለገሉበት ኬፕታወን ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ነው
በደቡብ አፍሪካ የፀረ አፓርታይድ ዘመቻ ጉልህ ሚና የነበራቸው ሊቀ ጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ ስርአተ ቀብራቸው ተፈጽሟል፡፡
ሊቀ ጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ በ90 ዓመታቸው ነበር ህይወታቸው ያለፈው፡፡
ቱቱ በኬፕታወን በሚገኘው ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የአስከሬን ሽኝት ስነ ስርዓት የተካሄደ ሲሆን በዚህ ፕሮግራም ላይ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዘዳንት ሲሪል ራማፎሳን ጨምሮ የሟች ቤተሰቦች እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
በስነ ስርዓቱ ላይ የዴዝሞንድ ቱቱ ባለቤት የነበሩት ኖማሊዞ እና ልጃቸው ምፎ ቱቱ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል፡፡
ልጃቸው ምፎ ቱቱ ባደረጉት ንግግር አባቴን ስለወደዳችሁት አመሰግናለሁ፣አባቴ የዓለም ነበር፣ፍቅራችንን ስለተጋራችሁን እናመሰግናለን ሲሉ ለታዳሚዎች ተናግረዋል፡፡
በኮሮና ቫይረስ ምክንያትም በአስከሬን ሽኝት እና ስርዓተ ቀብር ፕሮግራም ላይ የተገኙት 100 ሰዎች ብቻ መሆናቸውንም የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡
በአፓርታይድ ላይ ባደረጉት ሰላማዊ ተቃውሞ እንደፈረንጆቹ በ1984 የኖቤል የሰላም ሽልማት ማሸነፍ የቻሉት ሊቀ ጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ፤ ከአስር አመታት በኋላም የዚያን የጨለማ ዘመን ግፍና በደል በቁፋሮ ለማውጣት የተቋቋመ የእውነት እና የዕርቅ ኮሚሽን ሊቀመንበር በመሆን የዚያን አገዛዝ መጨረሻ መመልከት የቻሉ ታላቅ ሰው እንደነበሩ ይታወሳል፡፡
ሊቀ ጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ፤ ህይወታቸው ያለፈው ከካንሰር በሽታ ጋር ሊሆን እንደሚችልም የሊቀ ጳጳሱ ጽ/ቤት መግለጹን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ቱቱ በ1990ዎቹ መገባደጃ ላይ የፕሮስቴት ካንሰር እንዳለባቸው አውቀው የነበረ ሲሆን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከካንሰር ህክምናው ጋር ተያይዘው በሚመጡ በሽታዎችን በበርካታ አጋጣሚዎች ሆስፒታል ሲመላለሱ ቆይቷል፡፡
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ "የሊቀ ጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ ህልፈት በሀገራችን ነጻ የወጣችውን ደቡብ አፍሪካን ውርስ ለሰጡን ደቡብ አፍሪካውያን ትውልዶች ሌላው የሀዘን ምዕራፍ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።