አርሜኒያ እና አዘርባጃን በናጎርኖ-ካራባክ ጉዳይ የሰላም ስምምነት ላይ ደረሱ
በስምምነቱ መሰረት በሁለቱ መካከል የሩሲያ ሰላም አስከባሪ ጦር ገብቶ ለ5 ዓመታት ይቆያል ተብሏል
ስምምነቱ አርመናውያንን ያስቆጣ ሲሆን አዘርባጃን ደስተኛ መሆኗን ገልጻለች
አርሜኒያ እና አዘርባጃን በናጎርኖ-ካራባክ ጉዳይ የሰላም ስምምነት ላይ ደረሱ
አርሜኒያ እና አዘርባጃን የናጎርኖ-ካራባክን ውጊያ ለማቆም በሩሲያ ተስማምተዋል፡፡ ናጎርኖ-ካራባክን ለመገንጠል ሲካሔድ የነበረው እና 30 ሺህ ያክል ሰዎች የሞቱበት ውጊያ ቆሞ እ.ኤ.አ. በ1994 የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ግዛቷ በአርሜኒያ በሚደገፉ አርመናውያን ቁጥጥር ስር ነበረች፡፡
ከተኩስ አቁም ስምመነቱ በኋላ አልፎ አልፎ ግጭቶች ቢኖሩም እ.ኤ.አ. ካለፈው መስከረም 27 ጀምሮ በድጋሚ ከፍተኛ ጦርነት ውስጥ ገብተው ቆይተዋል፡፡
በናጎርኖ-ካራባክ ጉዳይ በሁለቱ ሀገራት መካከል ላለፉት ሳምንታት ሲደረግ የነበረውን ጦርነት ለማስቆም ተደጋጋሚ የተኩስ አቁም ስምምነቶች ቢፈረሙም ሳይከበሩ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ላይ አዘርባጃን ከፍተኛ ድል ማስመዝገቧን ተከትሎ ፣ በሩሲያ የተደረሰው ሰምምነት ተግባራዊ እንደሚሆን ይታመናል፡፡ ከፍተኛ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላት ሹሺ የተባለች ከተማም በአዘርባጃን ጦር እጅ ወድቃለች፡፡
በስምምነቱ መሰረት አርሜኒያ ከናጎርኖ-ካራባክ ድንበር ውጭ የያዘቻቸውን አንዳንድ የአዘርባጃን ይዞታዎች ለቃ ትወጣለች፡፡ ናጎርኖ-ካራባክን ከአርሜኒያ ጋር የሚያገናኘው መንገድ የሚገኝበትን የላቺን ግዛትም የአርመን ኃይል ለቆ መውጣት ይጠበቅበታል፡፡ በምትኩ 1,960 የሩሲያ ሰላም አስከባሪዎች እንዲገቡ እና ለአምስት ዓመታት እንዲቆዩ ተስማምተዋል፡፡
ናጎርኖ ካራባክን ከአርሜኒያ ጋር የሚያገናኘው መንገድ መጨናነቅ-ቅዳሜ ጥቅምት 28/2013 ዓ.ም
የትናንቱ ስምምነት አርመናውያንን ያላስደሰተ ሲሆን አዘርባጃን ደግሞ መደሰቷን ገልጻለች፡፡
“ለኔም ለሁላችንም ከባድ እጅግ በጣም ከባድ ውሳኔ ወስኛለሁ” ሲሉ የአርሜኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኒኮል ፓሺንያን በፌስቡክ ገጻቸው ገልጸዋል፡፡
ይህን ተከትሎ በርካታ አርመናውያን በዋና ከተማዋ ዬሬቫን ተቃውሟቸውን ለመግለጽ ወጥተዋል፡፡
“መሬታችንን አሳልፈን አንሰጥም” የሚል የቁጣ ድምጽ በማሰማት የተወሰኑ ሰልፈኞች ዋነኛውን የመንግስት ህንጻ ሰብረው ገብተዋል፡፡
የአዘርባጃን ፕሬዝዳንት ኢልሀም አሊዬቭ ደግሞ ስምምነቱን የድል ዜና አድርገው ነው የገለጹት፡፡ “ዛሬ ይህን ስምምነት ስፈርም በኩራት ነው! ለአዘርባጃን ህዝብ እንኳን ደስ አላችሁ” ብለዋል ፕሬዝዳንት አሊዬቭ፡፡
ሁለቱ ሀገራት እስረኞችን እና የሞቱ ሰዎችን አስከሬን ለመለዋወጥም ተስማምተዋል ነው የተባለው፡፡
አዘርባጃን ከትናንት በስቲያ ዝቅ ብሎ ሲበር የነበረ የሩሲያን ሄሊኮፍተር መትታ የጣለች ሲሆን ለዚህም ይቅርታ ጠይቃለች፡፡ በሄሊኮፍተሩ መመታት በውስጡ የነበሩ ሁለት ሰዎች መገደላቸውን የአሶሼትድ ፕሬስ ዘገባ ያመለክታል፡፡