ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ ያስከተለው ጦርነቱ የተለያዩ ሀገራትን ወዳሳተፈ ሰፊ ጦርነት እንዳያድግ ተሰግቷል
የተኩስ አቁም ስምምነቱን በመጣስ የናጎርኖ-ካራባክ ጦርነት ተባብሶ ቀጥሏል
ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ እያስከተለ የሚገኘው የናጎርኖ-ካራባክ ጦርነት በሩሲያ አሸናጋይነት ባለፈው ቅዳሜ ከምሽት ጀምሮ የሚተገበር ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርሶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በቀጣዩ ቀን በሙላት እንደተተገበረ የተነገረለት ስምምነቱ ከሁለተኛው ቀን ማለፍ አልቻለም፡፡ ለዚህም አዘርባጃን እና አርሜኒያ በመወነጃጀል ጣታቸውን ተቀሳስረዋል፤ ምንም እንኳን ለንጹሀን ተጎጂዎች ምንም ትርጉም ባይኖረውም፡፡ ሰኞ እለት ነበር የሩሲያው ዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጊ ላቭሮቭ ግጭቱ ዳግም መቀስቀሱን የተናገሩት፡፡
የአዘርባጃን መከላከያ ሚኒስቴር በሞስኮ በተደረሰው ስምምነት እስረኞችን እና የሟቾችን አስከሬኖች ለመለዋወጥ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለማክበር ሀገራቸው ዝግጁ እንደነበረች ገልጸዋል፡፡ የአዘሪ ኃይሎች ስምምነቱን እንደማይጥሱ በመግለጽ የአርሜንያ ኃይሎችን ከሰዋል፡፡
ሰብዓዊ ቀውስ፡ በአዘርባጃን ጋንጃ ከትልቅ ፍንዳታ በኋላ
ክሱን ውድቅ ያደረገችው አርሜኒያ አዘርባጃን “በደቡብ ፣ በሰሜን ፣ በሰሜን ምስራቅ እና ምስራቅ አቅጣጫዎች መድፍ በመተኮስ” ወታደራዊ እንቅስቃሴዋን እንደቀጠለች አስታውቃለች፡፡
ሰብዓዊ ቀውስ፡ በናጎርኖ-ካራባክ ፣ ስቴፓናከርት ውስጥ
ዓለም በኮቪድ-19 ቀውስ በተጠመደበት ወቅት የደራ ጦርነት ውስጥ የሚገኘው ቀጣና ከሰብዓዊ ቀውስ ባለፈ የተለያዩ ሀገራትን ወዳሳተፈ ሰፊ ጦርነት እንዳያድግ ተሰግቷል፡፡
በተለይ አካባቢው የነዳጅ ማስተላለፊያ እና የንግድ መስመር መሆኑ ስጋቱን ያባብሰዋል፡፡ በሶሪያ እና በሊቢያ በእጅ አዙር ጦርነት ውስጥ የሚገኙት ሩሲያ እና ቱርክ ተሳታፊ መሆናቸው ደግሞ የጦርነቱን አሳሳቢነት ያጎላዋል፡፡ ለሁለቱም ወገኖች የጦር መሳሪያ የምታቀርበው ሩሲያ በአርሜኒያ የጦር ሰፈር ያላት ሲሆን ቱርክ አዘርባጃንን በግልጽ ትደግፋለች፡፡ ኢራንም በዚያ አካባቢ የራሷ ፍላጎት አላት፡፡
ከ2 ሳምንታት በላይ የቆየው ጦርነቱ በናጎርኖ ካራባክ ብቻ በትንሹ የ532 በላይ ሰዎች ህይወት ተቀጥፏል፡፡
በናጎርኖ-ካራባክስቴፓናከርት፡ አርመናውያን በቤተክርስቲያንውስጥ ተጠልለው
አዘርባጃን 42 ንጹሃን ከመገደላቸው ውጭ በወታደሮቿ ላይ ስለደረሰው ጉዳት መረጃ አልሰጠችም የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ፒተር ማውረር ለሲኤንኤን እንዳሉት ከጦርነቱ ከባድነት ጋር በተያያዘ ሰራተኞች የሰብዓዊ አገልግሎት ስራቸውን ማከናወን እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡
በጦርነቱ በርካታ የመኖሪያ ቤቶች ወድመዋል ፤ 75 ሺህ ያህል ህዝብ ከመኖሪያ ቀዬው ተፈናቅሏል፡፡