የባንግላዲሽ ጦር አዛዥ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ስልጣን መልቀቃቸውን አረጋግጠዋል
ህዝባዊ ተቃውሞ የበዛባቸው የባንግላዲሽ ጠቅላይ ሚንስትር ወደ ሕንድ ኮበለሉ።
የእስያዊቷ ባንግላዲሽ ጠቅላይ ሚንስትር ሼክ ሀስና ላለፉት ሳምንታት ህዝባዊ ተቃውሞ ሲካሂድባቸው ቆይቷል።
ተቃውሞውን ለማብረድ የሀገሪቱ የጸጥታ ሀይሎች የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ ቢቆዩም ጠቅላይ ሚንስትሯ ስልጣን ለመልቀቅ ተገደዋል።
የ76 ዓመቷ የባንግላዲሽ ጠቅላይ ሚንስትር ሼክ ሀስና መንግስታቸው የሲቪል ሰርቪስ ቅጥር ኮታ ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ነበር ህዝባዊ ተቃውሞ የተነሳባቸው።
በዩንቨርስቲ ተማሪዎች የተጀመረው ይህ የህዝብ ተቃውሞ ቀስ በቀስ ሌሎች ወጣቶች እና የሀገሬው ህዝብ ሲቃወም ቆይቷል።
ከ96 በላይ ወጣቶች የተገደሉበት ይህ የህዝብ ተቃውሞ በርትቶ ጠቅላይ ሚንስትር ሼክ ሀስና ተገደው ወደ ጎረቤት ሀገር ሕንድ ተሰደዋል።
በሀገሪቱ የጦር አውሮፕላን ተሳፍረው ወደ ሰሜናዊ ሕንድ የተሰደዱት ጠቅላይ ሚንስትር ሀስና ስልጣናቸውን እንደለቀቁ የባንግላዲሽ ጦር አዛዥ እንደገለጹ ሲኤንኤን ዘግቧል።
የተቃውሞ ሰልፍ አስተባባሪ የሆነው አሲፍ መሀሙድ በበኩሉ ወጣቶች እና ተማሪዎች ወደ ዋና ከተማው ዳካ አደባባዮች እንዲወጡ እና ደስታቸውን እንዲገልጹ ጥሪ አቅርቧል።
በአጠቃላይ በዚህ ተቃውሞ 300 ሰዎች መገደላቸውን ኤኤፈፒ የፖሊስ እና ሀኪሞች ማህበርን መረጃ ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
ላለፉት 15 ዓመታት ባንግላዲሽን በጠቅላይ ሚንስትርነት የመሩት ሼክ ሀስና ባሳለፍነው ጥር ወር ላይ በተካሄደ ምርጫ ለአራተኛ ጊዜ ተመርጠው መንበረ ስልጣን ይዘው ነበር።