ህንድ ከዩክሬን ጦርነት ወዲህ ራሷን ከሩሲያ እንድታርቅ ከምዕራባውያን ከፍተኛ ተጽእኖ ሲደረግባት ቆይቷል
አሜሪካ ህንድ ከሩሲያ ጋር ያላት ግንኙነት ያሳስበኛል አለች።
አሜሪካ፣ ህንድ ዩክሬንን ከወረረችው ሩሲያ ጋር ያላት ግንኙነት እንደሚያሳስባት እንደገለጸችላት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ በትናትናው እለት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ ይህን ያሉት የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ እና የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭሊድሚር ፑቲን ስላደረጉት ስብሰባ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ነው።
ህንድ ከዩክሬን ጦርነት ወዲህ ራሷን ከሩሲያ እንድታርቅ ከምዕራባውያን ከፍተኛ ተጽእኖ ሲደረግባት ቆይቷል። ከሩሲያ መልካም የሚባል የቆየ ታሪካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት እንዳላት የምትጠቅሰው ህንድ እስካሁን ይህን የምዕራባውያን ጫና አልተቀበለችውም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ፣ሩሲያ በዩክሬን ልዩ ያለችውን ወታደራዊ ዘመቻ ከከፈተችበት ከፈረንጆቹ የካቲት 2022 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረጉት ጉብኝት በትናንትናው እለት ከፑቲን ጋር ተገናኝተዋል።
"ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ ስለምን እንዳወሩ ለማወቅ የሚሰጧቸውን መግለጫዎች እናያለን፤ ነገርግን ከሩሲያ ጋር ያላት ግንኙነት እንደሚያሳስበን ለህንድ አሳውቀናል" ብለዋል ቃል አቀባዩ።
ቃል አቀባዩ ሌሎች ሀገራትም ከሩሲያ ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት፣ ሩሲያ የተመድ ቻርተርን፣ ዩክሬንን ሉአላዊነት እና የግዛት አንድነት ማክበር እንዳለባት ግልጽ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
ሩሲያ በሶቬት ህብረት ጊዜ ጀምሮ የህንድ ዋነኛ የጦር መሳሪያ አቅራቢ ሀገር ነች። ነገርግን የዩክሬኑ ጦርነት የሩሲያን የጦር መሳሪያ የማቅረብ አቅም ስላዳከመው፣ ህንድ ሌሎች አማራጮችን እየፈለገች ነው።
አሜሪካ፣ ህንድ በእሲያ ፓሲፊክ የቻይና ተገዳዳሪ እንድትሆንላት ትፈልጋለች።
ምዕራባዊውን ሀገራት ፑቲንን ለማግለል ቢሞክሩም፣ ቻይና፣ ህንድ፣ በመካከለኛው ምስራቅ እና አፍሪካ ያሉ ኃይሎች እና የላቲን አሜሪካ ሀገራት ግንኙነታቸውን እያጠናከሩ ይገኛሉ።