ሰሜን ኮሪያ በአሜሪካ መሪነት እየተመሰረተ ያለውን “የእስያ ኔቶ” በዋዛ አልመለከተውም አለች
አሜሪካ ከደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ጋር የጀመረችው ግዙፍ ወታደራዊ ልምምድ የደቀነውን ስጋት ለመመከትም “ከባድ እርምጃ” እወስዳለሁ ስትል ዝታለች
ሶስቱ ሀገራት የፒዮንግያንግን የኒዩክሌር ፕሮግራምና የሚሳኤል ሙከራ በጋራ ለመግታት ካለፈው አመት ጀምሮ ወታደራዊ ልምምድ እያካሄዱ ነው
ሰሜን ኮሪያ፥ አሜሪካ ከደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ጋር “የእስያ ኔቶ”ን የመሰለ ወትደራዊ ጥምረት እየመሰረተች ነው ስትል ወቀሰች።
ሶስቱ ሀገራት የጀመሩት ግዙፍ ወታደራዊ ልምምድ ሀገራቱ ትብብራቸው እያደገ መሄዱን አመላካች መሆኑንም ነው የሀገሪቱ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ የዘገበው።
አሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ከሃሙስ ጀምሮ “የነጻነት ጥግ” የሚል ስያሜ የሰጡትን የጋራ ወታደራዊ ልምምድ እያደረጉ ነው።
የአሜሪካን አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ (ቲወዶር ሩዝቬልት)ን ጨምሮ የጦር አውሮፕላኖች እና መርከቦችን ያካተተው የጦር ልምምድ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በፒዮንግያንግ ጉብኝት ባደረጉ ማግስት ነው የተጀመረው።
ሶስቱ ሀገራት የሰሜን ኮሪያን የኒዩክሌር ፕሮግራምና የማያቋርጥ የሚሳኤል ሙከራ በጋራ ለማስቆም ባለፈው አመት በሜሪላንድ ካምፕ ዴቪድ ስምምነት ከደረሱ በኋላ ትብብራቸው ተጠናክሯል።
የሀገራቱን ወታደራዊ ልምምድ እንደ ጦርነት ዝግጅት የምትቆጥረው ፒዮንግያንግ አሜሪካ መራሹን የሶስትዮሽ ወታደራዊ ጥምረቱን በዋዛ እንደማትመለከተው ነው ያስታወቀችው።
ኬሲኤንኤን ጠቅሶ ሬውተርስ እንዳስነበበው ሰሜን ኮሪያ የኮሪያ ልሳነ ምድር ውጥረትን ያባብሳል ያለችውን የሶስትዮሽ ወታደራዊ ትብብር ለመግታት “ከባድ እርምጃ” እወስዳለሁ ብላለች።
አሜሪካ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓንን የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አካል የማስመሰል ሙከራዋንም ኮንናለች።
ለዚህም ለአብነት ያነሳችው ደቡብ ኮሪያ ወደ ዩክሬን የጦር መሳሪያዎችን እልካለሁ የማለቷን ጉዳይ ነው።
ሴኡል በቅርቡ ወደ ኬቭ የጦር መሳሪያዎችን እንደምትልክ የዛተችው የፒዮንግያንግና ሞስኮ “ጠላትሽ ጠላቴ ነው” ወታደራዊ ትብብር አሳስቦኛል በሚል ነበር።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን የተፈራረሙትን የወታደራዊ ስምምነት ተከትሎ ደቡብ ኮሪያ በሴኡል የሚገኙትን የሩሲያ አምባሳደር መጥራቷ ይታወሳል።
ደቡብ ኮሪያ እና አሜሪካ ፒዮንግያንግ በዩክሬን ጦርነት ጥቅም ላይ የሚውሉ የጦር መሳሪያዎችን ለሩሲያ እንደምትልክ ይገልጻሉ።
ሞስኮ እና ፒዮንግያንግ የሚቀርብባቸውን ወቀሳ ደጋግመው ውድቅ ማድረጋቸው ይታወቃል።