ባርባዶስ የእንግሊዟን ንግስት ከርዕሰ ብሔርነት በማስወገድ ሪፐብሊክ ሆና ተመሰረተች
የእንግሊዝ ልዑላውያን ባንዲራ ወርዶ በይፋዊ የሃገሪቱ ባንዲራ እንዲተካና እንዲውለበለብም ተደርጓል
ዴም ሳንድራ ማሶን የመጀመሪያዋ የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሃላ ፈጽመዋል
ከካሪቢያን ደሴቶች አንዷ የሆነችው ባርባዶስ ንግስት ኤልሳቤጥን ከርዕሰ ብሔርነት በማስወገድ ሪፐብሊክ ሆና ዛሬ ተመሰረተች፡፡
ለ55 ዓመታት የዘለቀው የንግስት ኤልሳቤጥ አገዛዝ እንዲያበቃ ያደረገችው ባርባዶስ ዴም ሳንድራ ማሶንን የመጀመሪያዋ የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት አድርጋ ሾማለች፡፡
የ72 ዓመቷ ሳንድራ የንግስት ኤልሳቤጥ ልጅ የዌልሱ ልዑል አልጋወራሽ አዛውንቱ ቻርለስ በተገኙበት ትናንት ምሽት የመጀመሪያዋ የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ሆነው በብሪጅ ታውን ከተማ ቃለ መሃላ ፈጽመዋል፡፡
ሚያ አሞር ሞትሌይ ደግሞ በርዕሰ መንግስትነት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዋል፡፡
እናታቸው ለግማሽ ምዕት ዓመት ይዘውት ከነበረው ስልጣን በሚወገዱበት ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት ልዑል አልጋወራሽ ቻርለስ የዲሴቲቷ ሃገር ዜጎች ላሳለፉት በግፍ የተሞላ የባርነት ህይወት እውቅና ሰጥተዋል፡፡
ሁኔታዎች ቢቀያየሩም አሁንም ከባርባዶስ እና ከህዝቦቿ ጋር ወዳጅ ሆነው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡
ቻርለስ በመጨረሻ የእድሜ ዘመናቸው ላይ የሚገኙትን ንግስት ኤልሳቤጥን ተክተው የንግስና አልጋው ወራሽ ናቸው፡፡
ባርባዶስን ቅኝ ለገዟት የእንግሊዝ ልዑላውያን ቤተሰቦች የመጨረሻ የ“ምስጋና” ቃል በአዲሷ ፕሬዝዳንት ዴም ሳንድራ ማሶን ከተሰጠ በኋላ የልዑላውያኑ ባንዲራ ወርዶ በሃገሪቱ እንዲተካ ተደርጓል፡፡
ፕሬዝዳንት ዴም ሳንድራ ከፈረንጆቹ 2018 ጀምሮ በንግስት ኤልሳቤጥ ተሾመው ሃገሪቱን በዋና ገዢነት ሲያስተዳድሩ ቆይተዋል፡፡
ባርባዶስን ሙሉ በሙሉ ከልዑላውያኑ አገዛዝ አላቆ በሪፐብሊክነት ለመመስረት ነጻ ከወጡበት ከ1960ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ነበር፡፡ ከፈረንጆቹ 1998 ጀምሮም አዲ ህገ መንግስት ማርቀቅን ጨምሮ ሪፐብሊኳን ለመመስረት የሚያስችሉ ስራዎች ተጀምረዋል፡፡
እነዚህ ጥረቶች ፍሬ አፍርተውም ነው ባርባዶስ ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ነጻ ከወጣች ከ55 ዓመታት በኋላ ሪፐብሊክ ሆና መመስረቷን አውጃ የመጀመሪያ ፕሬዝዳንቷን የሾመችው፡፡
ባርባዶስ እስከዛሬ ድረስ በቀጥታ በንግስቲቷ ስር ሆነው ከሚተዳደሩ 16 ሃገራት መካከል አንዷ ነበረች፡፡ አንቲጓ፣ ባርቡዳ፣ ባሃማስ፣ ቤሊዝ፣ ግራናዳ፣ ጃማይካ፣ ሴንት ኪትስ እና ኔቪስ፣ ሴንት ሉቺያ እና ሴንት ቪንሰንት ከነዚህ ሃገራት መካከል ናቸው፡፡