ባርባዶስ ከመጪው ዓመት ጀምሮ ንግስት ኤልሳቤጥን ከርዕሰ ብሔርነት ለማንሳት ወሰነች
ከቅኝ ግዛት ነጻ ከወጡ ወዲህ በርካታ ሀገራት ንግስቲቱን ከስልጣን ያወረዱ ሲሆን በዚህ እርምጃ የመጨረሻዋ ሞሪሽየስ ነች
ንግስት ኤልሳቤጥ ከሀገራቸው ብሪታንያ ዉጭ በአሁኑ ወቅት ካናዳን ጨምሮ የ15 ሀገራት ንግስት ናቸው
ባርባዶስ ከመጪው ዓመት ጀምሮ ንግስት ኤልሳቤጥን ከርዕሰ ብሔርነት ለማንሳት ወሰነች
ባርባዶስ የብሪታንያዋን ንግስት ኤልሳቤጥ ሁለተኛን ከርዕሰ ብሔርነት በማንሳት በሚቀጥለው ዓመት ሪፐብሊክ እንደምትሆን የሀገሪቱ መንግስት አስታወቀ፡፡ በዚህም ከሶስት አስርት ዓመታት ገደማ በኋላ ንግስቲቱን ከርዕሰ ብሔርነት በማንሳት ባርባዶስ የመጀመሪያዋ ሀገር መሆኗን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
የካሪቢያኗ ሀገር ባርባዶስ ጠቅላይ ገዥ ሳንድራ ማሶን ማክሰኞ ዕለት ባደረጉት ንግግር “የቅኝ ግዛት ወቅት ያለፈ ታሪካችንን ሙሉ በሙሉ ለመተው ጊዜው አሁን ነው” ብለዋል፡፡
ሀገሪቱ ከብሪታንያ ቅኝ ግዛት ነፃነቷን የተቀዳጀችበትን 55ኛ ዓመት እንደ አውሮፓውያኑ በቀጣዩ ዓመት ህዳር ወር በምታከብርበት ወቅት ሪፐብሊክ እንደምትሆን ነው ማሶን የገለጹት፡፡
ንግስት ኤልሳቤጥ እ.ኤ.አ. በ2018 ሳንድራ ማሶንን በቤተመንግሥታቸው ሲቀበሉ
የዩናይትድ ኪንግደም (ብሪታንያ) ንግስት ኤልሳቤጥ ከብሪታንያ በተጨማሪ አውስትራሊያ ፣ ካናዳ ፣ ኒው ዝላንድ እና ጃማይካን ጨምሮ ቀደም ሲል በብሪታንያ ቅኝ ግዛት ስር የነበሩ 15 ሀገራት ንግስትም ናቸው፡፡ ከነዚህ ሀገራት አንዷ የሆነችው ባርባዶስ እ.ኤ.አ በ1966 ከቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ ንግስቲቱ የሀገሪቱ ሕገ መንግሥታዊ ርዕሰ ብሔር ሆነው ቀጥለዋል፡፡
ይሁንና ባርባዶሳውያን ለረዥም ዓመታት ንግስቲቱ በሀገራቸው ላይ ያላቸው ስልጣን እንዲነሳ ሲጠይቁ መቆየታቸው በሲኤንኤን ዘገባ ተጠቁሟል፡፡
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞትሌ “ባርባዶሳውያን ባርባዶሳዊ ርዕሰ ብሔር እንዲኖር ይፈልጋሉ፡፡ ይህ እኛ ማን እንደሆንን እና ምን ማድረግ እንደምንችል የመጨረሻው የመተማመኛ መግለጫ ነው” ስለማለታቸው ማሶን ገልጸዋል፡፡
“ስለሆነም55 ኛው የነፃነት በአላችንን በምናከብርበት ጊዜ ባርባዶስን ሪፓብሊክ በማድረግ ወደ ሙሉ ሉዓላዊነት እንሸጋገራለን” ሲሉ በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡
ነፃነታቸውን ከተቀዳጁ በኋላ ባሉት ዓመታት በርካታ ሀገራት ንግስቲቱን ከርዕሰ ብሔርነት ያነሱ ሲሆን እ.ኤ.አ. በ 1992 ይህን እርምጃ የወሰደችው ሞሪሺየስ ንግስቲቱን በማንሳት የመጨረሻዋ ሀገር ነች፡፡