በሎንዶን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ ከእንግሊዝ ባለስልጣናት ጋር ባደረገው ውይይት ጨረታው መታገዱን አስታውቋል
በሎንደን የሚገኘው የኢትይጵያ ኢምባሲ እንዳስታወቀው በአጼ ቴዎድሮስ የንግስና ዘመን በእንግሊዞች ተዘርፈው የተወሰዱ ቅርሶች በፈረንጆቹ እስከ ነገ ሰኔ 17፣ 2021 ዓመት ድረስ የሚቆይ የሐራጅ ሽያጭ ማስታወቂያ ወጥቶባቸው ነበር።
ይሁንና ኢምባሲው ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የእንግሊዝ ባለስልጣናት ጋር ባደረገው ውይይት ጨረታው እንዲታገድ ማድረጉን ተገልጿል።
የእንግሊዝ መንግስት በሐራጅ ለመሸጥ ማስታወቂያ ያወጣባቸው ቅርሶች አጼ ቴዎድሮስ በመቅደላ ጦርነት በእንግሊዞች መሸነፋቸውን ተከትሎ ጦሩ ወደ ሎንደን ሲመለስ የዘረፋቸው መጽሀፍ ቅዱስ፤መስቀል፤ አልባሳት እና ሌሎች ከወርቅ እና ከዝሆን ጥርስ የተሰሩ ጌጣጌጦች ናቸው።
ይሁንና ኢምባሲው ባደረገው ውይይት እነዚህ ቅርሶች የኢትዮጵያ የከዚህ በፊቱ የአሁኑ እና የወደፊቱ ትውልድ ቅርሶች በመሆናቸው ወደ ኢትዮጵያ ሊመለስ ይገባል በሚል ለእንግሊዝ መንግስት ጥያቄ አቅርቧል።
በተደረገው ውይይትም እነዚህ ቅርሶች የወጣባቸው የሐራጅ ሽያጭ ማስታወቂያ የተሰረዘ ሲሆን ቅርሶቹ በቀጣይ ወደ ኢትዮጵያ የሚመለሱበትን መንገድ እንደሚያቻች ተጨማሪ ውይይቶች ማድረጉን እንደሚቀጥል ኢምባሲው አስታውቋል።
የመቅደላ ጦርነት በ1960 ዓ.ም አጼ ቴዎድሮስ የእንግሊዝ ዜጎችን በማሰራቸው ምክንያት እና እንግሊዝ ዜጎቿ እንዲለቀቁላት ያቀረበችው ጥሪ ምላሽ ባለማግኘቱ የተነሳ የተካሄደ ጦርነት መሆኑ ይታወሳል።
እንግሊዝም ወደዜጎቿን ለማስለቀቅ ወደ አጼ ቴዎድሮስ ጦር በመላክ ጦርነቱ የተካሄደ ሲሆን አጼ ቴዎድሮስ በጦርነቱ መሸነፋቸውን ተከትሎ እጅ ላለመስጠት እራሳቸውን እንዳጠፉ በባህሩ ዘውዴ የተጻፈው የኢትዮጵያ ታሪክ ያስረዳል።
እንግሊዞችም ንጉሱ እራሳቸውን ማጥፋታቸውን ተከትሎ ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስን ጨምሮ የንጉሱን የራስ ጸጉር፤ መጽሀፍት እና የተለያዩ ቅርሶችን ይዘው ወደ እንግሊዝ መመለሳቸው ይጠቀሳል።