ህብረቱ በጉዳዩ ላይ ለመምከር የሚስችል አስቸኳይ ስብሰባን ጠርቷል
ዳግም ተቀስቅሶ በእንግሊዝ እና በዌልስ በፍጥነት በመዛመት ላይ ባለው የኮሮና ወረርሽ ምክንያት የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት በእንግሊዝ ላይ ድንበር ዘጉ፡፡
አባል ሃገራቱ ከወደ እንግሊዝ የሚደረጉ የአየርም ይሁን የምድር ላይ እንቅስቃሴዎችን አገግደዋል፡፡
ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ አየርላንድ፣ ቤልጂዬም፣ ጣሊያን፣ ቡልጋሪያ፣ ፊንላንድ እና ዴንማርክ ይህን ካደረጉት ሃገራት መካከል ናቸው፡፡
የህብረቱ አባል ያልሆኑት ካናዳ፣ሳዑዲ አረቢያ፣ ሞሮኮ እና ቱርክም ይህንኑ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል እንደ ዩሮ ኒውስ ዘገባ፡፡
ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በድምሩ 30 ገደማ ሃገራት የእንቅስቃሴ እገዳውን ጥለዋል፡፡
ይህ ከእንግሊዝም ሆነ ወደ እንግሊዝ የሚደረጉ ድንበር ተሻጋሪ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴዎችን የሚያስተጓጉል ነው፡፡
እገዳው በመጪው የገና በዓል የምግብ እና ሌሎች ሸቀጦች አቅርቦት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖን ሊያሳድር እና የዋጋ ንረትን ሊፈጥር እንደሚችል ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንም ካቢኔያቸውን ለአስቸኳይ ስብሰባ ጠርተው እንደሚያወያዩ ገልጸዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ካውንስልም በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ የተቀናጀ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ውሳኔን እንደሚያሳልፍ አስታውቋል፡፡
እንግሊዝ ምንድነው የገጠማት?
የኮሮና ታማሚዎቿ ቁጥር ትናንት ብቻ በ35 ሺ 928 አዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች ጨምሯል፡፡ ይህ ባለፉት 7 ቀናት ከተመዘገበው የታማሚዎች ቁጥር በእጥፍ የሚበልጥ ነው፡፡ ላለፉት 28 ቀናት ታመው ነበር የተባለላቸው 326 የቫይረሱ ታማሚዎችም ሞተዋል፡፡ ይህም አጠቃላይ የሟቾቹን ቁጥር 67 ሺ 401 የሚያደርስ ነው፡፡
ይህ አዲስ ነው በተባለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የመጣ ነው፡፡ ቫይረሱ ከቀድሞው በተለየ በ70 በመቶ ያህል ከሰው ወደ ሰው ሊተላለፍ ይችላል እንደ ጤና ሚኒስትሩ ማት ሃንኩክ ገለጻ፡፡
ቫይረሱ ሎንደንን ጨምሮ በደቡብ ምስራቃዊ እንግሊዝ በፍጥነት እየተዛመተ ነው፡፡ ሆኖም ስለ ገዳይነቱ ደረጃ እና አዲስ በመዘጋጀት ላይ ያሉትን ክትባቶች መላመድ ስለመቻሉ የታወቀ ነገር የለም፡፡
በዚህም ምክንያት እንግሊዝ ጥብቅ የሚባሉ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ወስዳለች፡፡ በመጪው ገና ሊኖር የሚችለውን ከፍተኛ የህዝብ መሰባሰብ ለማስቀረት እንደሚያስችሉ የታመነባቸውን የደረጃ 4 ክልከላዎችንም ተግባራዊ አድርጋለች እንደ ቢቢሲ ዘገባ፡፡