በቀጣዮቹ 10 ቀናት በሚኖር ከባድ ዝናብ ቅጽበታዊ ጎርፍ እና ሌሎች አደጋዎች ሊያጋጥሙ ይችላሉ ተባለ
እስካሁን ደቡብ ኦሮሚያ እና ሶማሌ አካባቢዎች ክረምቱ ያልገባባቸው ቦታዎች ናቸው
የአዋሽ እና የዓባይ ተፋሰስ አካባቢዎች ለጎርፍ አደጋዎች ሊጋለጡ እንደሚችሉም ተነግሯል
በቀጣዮቹ 10 ቀናት በሚኖር ከባድ ዝናብ ቅጽበታዊ ጎርፍ እና ሌሎች አደጋዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ብሔራዊ ሜቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ አሳሰበ።
ኤጀንሲው በቀጣዮቹ ቀናት አብዛኞቹ የክረምቱ ዝናብ ተጠቃሚ የሆኑ አካባቢዎች አሁንም ዝናብ ማግኘታቸውን ይቀጥላሉ ብሏል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ የአየር ሁኔታ እና የአየር ጸባይ ትንበያ ባለሙያ አቶ ታምሩ ከበደ በቀጣዮቹ 10 ቀናት በሚኖር ከባድ ዝናብ ቅጽበታዊ ጎርፍ እና ሌሎች አደጋዎች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
ባለሙያው የአዋሽ እና የዓባይ ተፋሰስ አካባቢዎች ከመደበኛው የበለጠ ዝናብን ሊያገኙ ይችላሉም ነው ያሉም፡፡
ይህም ለቅጽበታዊ ጎርፍ አደጋ ሊያጋልጣቸው እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡
ወቅቱ ዝናብ ዘንቦ መሬቱ በቂ እርጥበት ያገኘ እና መሬቱ ውሃ የጠገበበት ጊዜ በመሆኑ አሁን ላይ ዝናብ ሲዘንብ በቀላሉ ወደ ጎርፍነት ተቀይሮ ወንዞችም በቀላሉ እንደሚሞሉ ተናግረዋል።
በዚህም ምክንያት በአባይ እና አዋሽ ተፋሰሶች ስር ባሉ የወንዝ ዳርቻ የሚኖሩ ዜጎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ባለሙያው አሳስበዋል።
በቂ ዝናብ በማያገኙ አካባቢዎች በተለይም በአፋር ክልል ስፍራዎች በደጋማ አካባቢዎች በሚዘንብ ከባድ ዝናብ ምክንያት ቅጽበታዊ ጎርፍ የመድረስ እድሉ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችልም ነው ባለሙያው የተናገሩት።
አሁን ላይ አፈሩ ውሃ የመያዝ መጠኑ የሚቀንስ መሆኑን ተከትሎ በተለይም በመካከለኛው ኦሮሚያ እና በደቡብ ክልል አንዳንድ ቦታዎች የመሬት መንሸራተት አደጋ ሊያጋጥም እንደሚችልም አስጠንቅቀዋል።
በተዳፋት ስፍራዎች እና በወንዝ ዳርቻዎች የሚኖሩ ዜጎች በተለይም ተፋሰስ ያለባቸው የርብ፣ የፎገራ፣ የጣና እና ሌሎች ስፍራዎች በጎርፍ የመጥለቅለቅ አደጋዎች ሊከሰቱ ስለሚችሉ ህብረተሰቡ እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አደጋው የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ከወዲሁ ዝግጅት እንዲያደርጉ ሲሉም ነው አቶ ታምሩ ያስጠነቀቁት።
የኤጀንሲው የዘንድሮ ክረምት ትንበያ እንደሚያስረዳው አብዛኛው የአገሪቱ ቦታዎች መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ ዝናብ በማግኘት ላይ ናቸው።
ሰሜናዊ አጋማሽ፣ መካከለኛው እና ምዕራብ አጋማሽ፣ መካከለኛው ኢትዮጵያ አካባቢዎች ከአማካኝ በላይ ዝናብ ሲያገኙ ሰሜን ምስራቅ፣ የደቡብ ደጋማ ስፍራዎች፣ ምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች መካከለኛ ዝናብ በማግኘት ላይ ናቸው።
ይሁንና የደቡብ፣ የሶማሌ፣ የደቡብ ኦሮሚያ ቆላማ ቦታዎች እንዲሁም ደቡባዊ የደቡብ ክልል አካባቢዎች አሁን ላይ መደበኛ ዝናብ እያገኙ አይደለም።
የደቡባዊ ምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ክረምቱ ቀድሞ የሚገባባቸው አካባቢዎች ሲሆኑ የክረምት ሁኔታው ቀስ በቀስ ወደ መካከለኛው፣ ምስራቅ፣ ሰሜን እና ሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ እየተስፋፋ እንደሚሄድ አል ዐይን ከኤጀንሲው ያገኘው መረጃ ያስረዳል።