በከተማዋ ለ2 ሳምንታት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል
በከተማዋ ለ2 ሳምንታት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል
ትናንት ቤሩትን ባናወጠው ፍንዳታ ከአንድ መቶ የሚልቁ ሰዎች መሞታቸው መሞታቸው መረጋገጡን የሃገሪቱ የዜና አገልግሎት ዘገበ፡፡
ፍንዳታው በአካባቢውና በቅርብ ርቀት ስፍራዎች ጭምር ከፍተኛ ሰብዓዊ ጉዳት ማድረሱን ለዜና አገልግሎቱ የገለጹት የሃገሪቱ ቀይ መስቀል ኃላፊ ከ4 ሺ በላይ ሰዎችን ለጉዳት ስለመዳረጉም ለሃገሪቱ የዜና አገልግሎት ተናግረዋል፡፡
የአደጋው ሰላባዎች ገና በመፈለግ ላይ መሆናቸውን ተከትሎ የሟቾቹና የተጎጂዎቹ ቁጥር ከዚህም በላይ ሊጨምር ይችላል፡፡
ቤሩትን ያራደው ፍንዳታ 3 ነጥብ 3 ሬክተር ስኬል ልኬት ያለውን የመሬት መንቀጥቀጥ ያህል አካባቢውን እንዳንቀረቀበው ነው መረጃዎች ያመለከቱት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃሰን ዲያብ የከፋ የተባለው ፍንዳታ በከተማዋ ወደብ በሚገኝ አንድ መጋዘን ተከማችቶ በቆየ ከ2 ሺ 750 ቶን በላይ የአሞኒዬም ናይትሬት ኬሚካል ምክንያት ማጋጠሙን ተናግረዋል፡፡
ሊባኖስ በከፍተኛ ምጣኔ ሃብታዊ ድቀት ውስጥ እንዳለች የዘገቡ ዓለም አቀፍ ብዙሃን መገናዎች አደጋውን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሲሉ ነው የገለጹት፡፡
በፕሬዝዳንት ሚሼል አውን የተጠራው የሃገሪቱ ሚኒስትሮች ምክር ቤት (ካቢኔ) ባብዳ ቤተመንግስት ለአስቸኳይ ስብሰባ ተቀምጦ ነው ያረፈደው፡፡ ካቢኔው በስብሰባው ፍንዳታውን በተመለከተ በሃገሪቱ የመከላከያ ምክር ቤት የቀረበለትን ጥናት የተመለከተ ሲሆን የቤሩትን “የአደጋ ከተማ”ነት አውጇል፡፡
በዚህም ፍንዳታው ካጋጠመበት ከትናንትናው ዕለት የሚጀመርና ለቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ በስብሰባው ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
የአደጋውን መንስዔ የሚመረምር ኮሚሽን የተቋቋመም ሲሆን ኮሚሽኑ የደረሰበትን በቀጣዮቹ 5 ቀናት ውስጥ እንዲያሳውቅና ከፍንዳታው ጋር በተያያዘ ጥፋተኛ ሆነው በሚገኙ ላይ ከፍተኛ የተባሉ የቅጣት እርምጃዎች ይወሰዳሉም ተብሏል፡፡
አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍ ለሆስፒታሎች እና የነፍስ አድን ስራን ለሚሰሩ የአስቸኳይ ጊዜ ሰራተኞች እንዲደረግም በስብሰባው ተወስኗል፡፡
ቤሩት የገጠማትን ዱብዕዳ መቋቋም ትችል ዘንድ ሃገራት በደረሰው ችግር ሃዘናቸውን እየገለጹ ነው፡፡
በፍንዳታ ማዘናቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ “ጸሎቴ እና ሀሳቤ ከሊባኖ ነዋሪዎች ጋር ነው። በሊባኖስ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ከቆንስላችን ጋር ግንኙነት እንድትፈጥሩ በእጅጉ አበረታታለሁ። እንደዚህ ባለው አስከፊ ጊዜ መተጋገዝ አስፈላጊ ነው።” የሚል መልዕክትን በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጻቸው ጽፈዋል፡፡
የተባበሩት አረብ ኤሚሬትን ጨምሮ ጥቂት የማይባሉ የአረብ ሃገራትም ከቤሩት ጎን መቆማቸውን ገልጸዋል፡፡ የፈረንሳይ የህክምና ቡድን አባላት ወደ ከተማይቱ ያቀኑ ሲሆን ኩዌትም የእርዳታ አውሮፕላንን ልካለች፡፡