ቤንዜማ ስለፍልስጤም ድምጹን ማሰማቱ በሽብርተኝነት አስጠርጥሮታል
የፈረንሳይ ፖለቲከኞች ቤንዜማ “ከሙስሊም ወንድማማቾች ቡድን ጋር ጥብቅ ግንኙነት አለው” በማለት ዜግነቱን እንዲነጠቅም እየጠየቁ ነው
የቤንዜማ ጠበቃ ግን ውንጀላውን በማጣጣል ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እወስደዋለሁ ብለዋል
ፈረንሳዊው የእግር ኳስ ተጫዋች ካሪም ቤንዜማ በጋዛ ስለሚገኙ ፍልስጤማውያን የሰጠው አስተያየት የሀገሩን ፖለቲከኞች አስቆጥቷል።
የባሎንዶር አሸናፊውና የቀድሞው የሪያል ማድሪድ ተጫዋች በኤክስ(ትዊተር) ገጹ ላይ በጋዛ ባልተመጣጠነ የቦምብ ጥቃት ህጻናት እና ሴቶች እያለቁ ነው ማለቱ ነው ተቃውሞ ያስነሳበት።
የፈረንሳይ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ጀራልድ ዳርማኒን ከሲኒውስ ቻናል ጋር ባደረጉት ቆይታ ቤንዜማ በግብጽ ከታገደው “ሙስሊም ወንድማማቾች ጋር ጥብቅ ግንኙነት ነበረው” ማለታቸውን ፍራንስ 24 አስነብቧል።
የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባሏ ናዲን ሞራኖም “ቤንዜማ የሃማስ ፕሮፖጋንዳ አስፈጻሚ ነው” ብለዋል።
የፈረንሳይ ፓርላማ አባል የሆኑት ቫልሪ ፓውሊ በበኩላቸው ካሪም ቤንዜማ የፈረንሳይ ዜግነቱ እንዲነጠቅ ጠይቀዋል።
የተጫዋቹ ጠበቃ ሁጌስ ቪገር ግን “ይህ ሀሰት ነው፤ ካሪም ቤንዜማ ከዚህ ድርጅት (ሙስሊም ወንድማማቾች) ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለውም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
“ቤንዜማ በጋዛ በንጹሃን ላይ እየተፈጸመ ያለውን አንዳንዶች የጦር ወንጀል በማለት የሚጠቅሱትን ነው ያወገዘው፤ የቀረበበት ውንጀላም መሰረተ ቢስ ነው” ብለዋል።
የፈረንሳይ የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ጀራልድ ዳርማኒን ላይ ክስ ለመመስረትም በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አክለዋል።
ካሪም ቤንዜማ ከትውልደ አልጀሪያውያን ወላጆቹ በፈረንሳይ ሊዮን በፈረንጆቹ 1987 ነው የተወለደው።
የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን ኮከቡ ቤንዜማ በሪያል ማድሪድ የ14 አመት ቆይታው አምስት የሻምፒዮንስ ሊግ፣ አራት የላሊጋ እና ሶስት የኮፓዴላሬ ዋንጫዎችን አንስቶ ወደ ሳኡዲው ክለብ አል ኢትሃድ አቅንቷል።