ሞ ሳላህ በጋዛ የሚፈጸመው “ጭፍጨፋ” እንዲቆም ጥሪ አቀረበ
ግብጻዊው የሊቨርፑል አጥቂ ሁሉም ነገር በተዘጋጋባት ጋዛ የሰብአዊ እርዳታ በፍጥነት መቅረብ አለበት ብሏል
ግብጽ በራፋህ የድንበር መተላለፊያ በኩል የሰብአዊ ድጋፍ እንዲያልፍ መፍቀዷ ተነግሯል
የሊቨርፑሉ አጥቂ ሞሃመድ ሳላህ በጋዛ እየተፈጸመ ያለውን “ጭፍጨፋ” እንዲቆም ጥሪ አቅርቧል።
የ31 አመቱ ግብጻዊ በጋዛ የተቋረጡ አገልግሎቶች እንዲመለሱና የሰብአዊ ድጋፍም በፍጥነት እንዲቀርብ ነው የጠየቀው።
“በእንዲህ አይነት ሁኔታ ማውራት ከባድ ነው፤ በጣም ልብ የሚሰብሩ የጭካኔ ተግባራትን ተመልክተናል” ያለው ሞ ሳላህ፥ የተከበረው የሰው ልጅ ህይወት መጠበቅ እንጂ መጨፍጨፍ የለበትም ብሏል።
ሳላህ ከ62 ነጥብ 7 ሚሊየን ተከታይ ባለው የኢንስታግራም ገጹ ባስተላለፈው መልዕክት በጋዛ ያለው ሁኔታ በየቀኑ ይበልጥ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ገልጿል።
ሀገሩ ግብጽም ፍልስጤማውያንን ውሃ፣ ነዳጅና መብራት በማሳጣት ወደ ሲናይ በርሃ እንዲሰደዱ የማድረግ የእስራኤልን ውጥን ውድቅ አድርጋለች።
ፍልስጤማውያንን ከጋዛ ወደ ግብጽ እንዲሰደዱ ማድረግ ከእስራኤል ጋር ጦርነት ውስጥ ያስገባኛልም ነው ያለችው።
በቴል አቪቭ የሚገኙት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለ12 ቀናት ሁሉም ነገር በተቆለፈባት ጋዛ የሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ ከእስራኤል ጋር መስማማታቸውን ገልጸዋል።
ሰብአዊ ድጋፍ ጭነው በግብጽ እና ጋዛ ድንበር በሆነው ራፋህ የሚገኙ ከ100 በላይ ተሽከርካሪዎችም ከነገ ጀምሮ ወደ ጋዛ መግባት ይጀምራሉ ነው የተባለው።
በሃማስ እና እስራኤል ጦርነት እስካሁን ከ3 ሺህ 400 በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።