ትዊተር (ኤክስ) አዲስ አካውንት ለመክፈት 1 ዶላር ማስከፈል ጀመረ
የኤለን መስክ ኩባንያ ክፍያ ያልፈጸሙ ሰዎች መረጃዎችን ከማየት ያለፈ ተሳትፎ አይኖራቸውም ብሏል
ውሳኔው ሀሰተኛ አካውንቶችን ለመቀነስና የኩባንያውን ገቢ ለማሳደግ እንደሚያግዝ ታምኖበታል
ኤክስ (የቀድሞው ትዊተር ) አዳዲስ ደንበኞቹን አመታዊ ክፍያ ማስከፈል ጀመረ።
የማህበራዊ ትስስር ገጹ በኒውዝላንድ እና ፊሊፒንስ የጀመረው የ1 ዶላር አመታዊ ክፍያ በሌሎች ሀገራትም በቀጣይ ይተገበራል ተብሏል።
አመታዊውን ክፍያ የፈጸሙ ሰዎች መረጃዎችን ማጋራት (ትዊት ማድረግ)፣ አስተያየት መስጠት፣ የሌሎች ሰዎችን መረጃ ማጋራት እና ሌሎች አገልግሎቶችን ማግኘት ይችላሉ።
ክፍያውን የማይፈጽሙት ግን መረጃዎችን ከማየት ያለፈ ተሳትፎ አይኖራቸውም ነው ያለው የኤለን መስኩ ኩባንያ ኤክስ።
ውሳኔው ሀሰተኛ አካውንቶች (ስፓም እና ቦት) ለመቀነስ እንደሚያግዝም አስታውቋል።
ባለሙያዎች ግን የኩባንያውን ገቢ ከማሳደግ የዘለለ የሀሰተኛ መረጃ ልውውጥ እና አካውንቶችን በመቀነስ ረገድ የረባ ለውጥ ያመጣል ብለው አያምኑም።
ለዚህም ኤክስ በወር በ11 ዶላር በማስከፈል የአካውንት ትክክለኛነት ማረጋገጫ ሰማያዊ ምልክት መስጠት ቢጀምርም ሀሰተኛ አካውንቶች አልቀነሱም የሚለውንም መከራከሪያ አድርገው ያቀርቡታል።
በ44 ቢሊየን ዶላር ትዊተርን የገዙት ኤለን መስክ የኩባንያውን ትርፋማነት ለማሳደግ የተለያዩ አገልግሎቶችን በክፍያ መስጠት ከጀመሩ ወራት እየተቆጠሩ ነው።
የአለማችን ቀዳሚው ቱጃር ባለፈው ወር ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚንን ኔታንያሁ ጋር ባደረጉት ምክክር ሁሉንም የኤክስ ተጠቃሚ ለማስከፈል ማቀዳቸውን መናገራቸው የሚታወስ ነው።