ካሪም ቤንዜማ በዓመት 200 ሚልዮን ዩሮ ክፍያ ለአል ኢትሀድ ፈረመ
ቤንዜማ ከ14 ዓመታት በኋላ ሪያል ማድሪድን በመልቀቅ የሳውዲ አረቢያውን አል ኢትሀድ በይፋ ተቀላቅሏል
የአል ትሃድ ፕሬዝዳንት "የወቅቱን የባሎን ዶር አሸናፊ ማስፈረም ለዚህ ልዩ ክለብ ታሪካዊ ነው" ብለዋል
ፈረንሳዊው የፊት መስመር አጥቂ ካሪም ቤንዜማ የሳዑዲ አረቢያው አል ኢትሃድ የእግር ኳስ ክለብን በይፋ ተቀላቀለ።
ካሪም ቤንዜማ በሳውዲ አረቢያው አል ኢትሀድን በ200 ሚሊየን ዩሮ ዓመታዊ ክፍያ የተቀላቀለ ሲሆን፤ በፈረንጆቹ እስከ 2026 የሚያቆየውን የሶስት አመት ኮንትራት ተፈራርሟል።
ቤንዜማ አል ትሃድን መቀላቀሉን ተከትሎ በሰጠው አስተያየት "በአዲስ ሊግ አዲስ ፈተናን ለመጋፈጥ ጓጉቻለሁ” ሲል ተናግሯል።
የአል ኢትሃድ ፕሬዝዳንቱት አንማር አል ሀይሊ በበኩላቸው፤ "የወቅቱን የባሎን ዶር አሸናፊ ማስፈረም ለዚህ ልዩ ክለብ ታሪካዊ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
ካሪም ቤንዜማ ከ14 ስኬታማ አመታት በኋላ ከሪያል ማድሪድ ጋር መለያየቱን ክለቡ ባሳለፍነው ሳምንት ማረጋገጡ ይታወሳል።
ከሊዮን በፈረንጆቹ 2009 ማድሪድን የተቀላቀለው ካሪም ቤንዜማ፥ 647 ጨዋታዎችን አድርጎ 353 ጎሎችን አስቆጥሯል።
በዚህም 450 ጎሎችን ካስቆጠረው ክርስቲያኖ ሮናልዶ በመቀጠል የሪያል ማድሪድ የምንጊዜም ሁለተኛ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋች መሆን ችሏል።
አምስት የሻምፒዮንስ ሊግ እና አራት የላሊጋ ጨምሮ 25 ዋንጫዎችን ያነሳው ቤንዜማ፥ ባለፈው አመት ማድሪድን ለሻምፒዮንስ ሊግ ድል በማብቃቱ የባሎንዶር ተሸላሚ እንደነበር አይዘነጋም።
ፈረንሳዊው አጥቂ ከሎስ ብላንካዎቹ ጋር መለያየቱን ተከትሎ ወደ ሳኡዲ አረቢያ እንደሚያመራ ተነግሮ ነበር።
የ35 አመቱ ተጫዋች ለአል ኢትሃድ ክለብ የሁለት አመት ኮንትራት እንደሚፈርም የሳኡዲው ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ አል አክባሪያ መዘገቡም ይታወሳል።