ወደቡ ዛሬ ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ ኮንቴይነሮችን ከመርከብ በማራገፍ ነው ስራውን በይፋ የጀመረው
የበርበራ ወደብ በይፋ ስራ ጀመረ፡፡
የወደቡ የመጀመሪያ ዙር ማስፋፊያ የኮንቴይነር ተርሚናል ዛሬ የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ልዑካን፣የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ እና የዲፒ ወርልድ ዳይሬክተር ሱልጣን ቢን ሱለይማን በተገኙበት በይፋ ስራ ጀምሯል፡፡
ወደቡ በዲፒ ወርልድ የ51%፣ በሶማሊላንድ የ30% እና በኢትዮጵያ የ19% ባለቤትነት የተያዘ ነው፡፡
የወደቡ ተርሚናል ኮሪደር የመጀመሪያ ዙር የማስፋፊያ ፕሮጀክት 500 ሺህ ኮንቲነሮችን የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን በአመት አንድ ሚሊዬን ኮንትነሮችን ማስተናገድ ይችላል ተብሏል፡፡
ክብደት ማንሻ ዘመናዊ ክሬኖች እንደተገጠሙለትና ከዛሬ ጀምሮ ግዙፍ መርከቦችን በማስተናገድ ለቀጠናው በተለይ ለኢትዮጵያ ትልቅ ጥቅም እንዳለው ተገልጿል።
የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ በወደቡ ይፋዊ ስራ ማስጀመሪያ ስነ ስርአት ላይ ወደቡ የ10 ዓመት ሃገራዊ የምጣኔ ሃብት ውጥኖችን ለያዘችው ኢትዮጵያ እድገት ትልቅ ሚና አለው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወጪና ገቢ ንግድን ለማሳደግ ወደቦችን ማልማትና መጠቀም አስፈላጊ ነው ያሉም ሲሆን የበርበራ ወደብ መከፈት የጎላ ጥቅም እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው የወደቡ የመጀመሪያው ዙር ተርሚናል ስራ መጀመር በቀጠናው የኢኮኖሚ ውህደትን ከፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
በተለይ በየጊዜው እያደገ የሚገኘውን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሳለጥ በበርበራ ወደብ ላይ ለሚደረገው ስራ ኢትዮጵያ እንደምትካፈልም ነው የገለጹት።
ሚኒስትሩ አክለው ከበርበራ ወደብ ኢትዮጵያ በተለይ የሶማሊ ክልል ተጠቃሚ እንደሚሆን ገልፀው፣ ኢትዮጵያ ከበርበራ -ጅግጅጋ- ድሬዳዋ-ኤረር- ሚኤሶ መንገድ በመገንባት ጅግጅጋንና ድሬዳዋን ከበርበራ ወደ ምስራቅ ኢትዮጵያ የኮንቴይነር መዳረሻ ይሆናሉ ብለዋል።
የሶማሊ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሙስጠፋ ሙሃመድ በበኩላቸው የሶማሊላንድ ልማትና እድገት የኢትዮጵያ በተለይ የሶማሊ ክልል እድገት እንደሆነ ጠቁመው፣ የበርበራ ወደብ ለቀጠናው ህዝብ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።
የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሳ ቢሂ በበኩላቸው ለኢትዮጵያ በተለይ ለሶማሊ ክልል ደረጃውን የጠበቀ የወደብ አገልገሎት እንደሚሰጡና ከወደብ የሚወርዱ እቃዎች በሰላም ወደ መዳረሻቸው እንዲደርሱ ይደረጋል ብለዋል።
በመጨረሻም የበርበራ ወደብ ዛሬ ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ ኮንቲነሮችን ከመርከብ በማራገፍ ስራውን በይፋ ጀምሯል።
ዲፒ ወርልድ በበርበራ ወደብ የሚገለገሉ ኢትዮጵያውያን ነጋዴዎች የሚጠቀሙበትን አዲስ የበይነ መረብ የግብይት ስርዓት በቅርቡ ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡