ኢትዮጵያ ከዲፒ ወርልድ ጋር የሎጂስቲክስ ኩባንያ ለማቋቋም ስምምነት ተፈራረመች
በርበራ ወደብን ከኢትያጵያ ጋር የሚያገናኘው መንገድ በያዝነው ዓመት መጨረሻ እንደሚመረቅ ይጠበቃል
ዲፒ ወርልድ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ የሎጂስቲክስ መሰረተ ልማት እንደሚገነባ ተገልጿል
የዱባዩ ዓለም አቀፍ የሎጂስቲክስ ተቋም (ዲፒ ወርልድ) እና ኢትዮጵያ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ዛሬ በአዲስ አበባ ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የኢትዮጵያ ትራንስፖርት ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ እና የዲፒ ወርልድ ስራ አስፈጻሚ ሱልጣን አህመድ ቢን ሱለይማን ተፈራርመዋል።
በዚህ ስምምነት መሰረት ዲፒ ወርልድ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ በርበራ ወደብ ለኢትይጵያ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን የሎጂስቲክስ መሰረተ ልማቶችን የሚገነባ ሲሆን ኢትዮጵያ መሰረተ ልማቶቹ እንዲገነባ ድጋፍ ታደርጋለች።
ሁለቱ ወገኖች በጋራ የሎጂስቲክስ ኩባንያ ሊያቋቁሙ እንደሚችሉም በስምምነቱ ላይ ተገልጿል።
ይህ የጋራ ሎጂስቲክስ ኩባንያ የኢትዮጵያ ምርቶች በበርበራ ወደብ በኩል ወደ ተለያዩ የዓለማችን አገራት መዳረሻ ገበያዎች እንዲደርሱ የሚያስችሉ ስራዎችን የሚያከናውን ይሆናል።
እንዲሁም ኢትዮጵያ የምትፈልጋቸው የውጭ ምርቶችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት በበርበራ ወደብ አድርገው ወደ አገር ውስጥ እንዲሰራጩ ያደርጋልም ተብሏል።
ዲፒ ወርልድ ከሚሰራቸው ተጨማሪ ስራዎች መካከልም ገዢ እና ሻጭ ኩባንያዎች የሚገለገሉባቸው ማከማቻ መጋዘኖችን ፣ የኤሌክትሮኒክስ መገበያያ መሰረተ ልማቶችን ፣ መንገዶችን እና ሌሎች የትራንስፖርት ማጓጓዣ አማራጮች ማስፋት ናቸው።
የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳይማዊት ሞገስ በስምምነቱ ወቅት እንዳሉት ይህ ስምምነት በጅቡቲ በኩል ብቻ ተወስኖ የነበረው የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ሌላ አማራጭ እንዲኖረው የሚያስችል ነው ብለዋል።
ይህ ስምምነት ኢትዮጵያ ይፋ ካደረገቸው የ10 ዓመት የትራንስፖርት ማስተር እቅድ ጋር ተመጋጋቢ መሆኑንም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
የዲፒ ወርልድ ስራ አስፈጻሚ ሱልጣን አህመድ ቢን ሱሌይማን በበኩላቸው ዲፒ ወርልድ የደረቅ ወደብ ፣ መጋዝኖች፣ የኮንቴይነሮች ማከማቻና ማቀዝቀዣዎችን ጨምሮ የምርት ጭነት ማሳለጫዎችን እና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶችን እንደሚገነባ ገልጸዋል።
በርበራ ወደብን ከኢትያጵያ ጋር የሚያገናኘው ዋጃሌ የመንገድ ፕሮጄክት በመገንብት ላይ ሲሆን በያዝነው ዓመት መጨረሻ ወራት እንደሚመረቅ ይጠበቃል።
ዲፒ ወርልድ በያዝነው ዓመት በ 442 ሚሊዮን ዶላር የበርበራ ወደብ ማስፋፊያ ግንብታን በማካሄድ ላይ መሆኑን የገለጸ ሲሆን ግንብታው ሲጠናቀቅ የወደቡን የመጫን አቅም ወደ 500 ሺህ ቶን ከፍ እንደሚያደርገው ገልጿል።